ፖምፔዮ በግድቡ ዙሪያ የሚካሄደው ውይይት በቅርቡ መቋጫ እንደሚያገኝ ጠቆሙ

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፒዮ

የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአሜሪካው አቻቸው ማይክ ፖምፔዮ ጋር ዛሬ ከሰዓት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ፤ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል ያሉ ሲሆን፤ ከ1930ዎቹ ጀምሮ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሲያካሂዱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በአሜሪካዋ ዋሽንግተን ዲ.ሲ በርካታ ቁጥር ያለው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ መኖሩን የጠቆሙት ፖምፒዮ በዛሬው መግለጫቸው በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እና በመጪው ምርጫ ላይ የአገራቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ

ፕሬዝደንት ትራምፕ ሦስቱንም አገራት ሊያስማማ የሚችል ስምምነት እንዲፈጠር ቅድሚያ የሰጡት ጉዳይ ነው ብለዋል ማይክ ፖምፔዮ።

የግድቡ ግንባታ በአሜሪካ የገንዘብ ሚንስትር እና በዓለም ባንክ አደራዳሪነት ሲካሄድ መቆየቱን እና የየአገራቱ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ወደ ዋሽንግተን በተደጋጋሚ መጓዛቸውን አስታውሰዋል።

ፖምፒዮ "የመግባቢያ ነጥቦች እየተጠናቀቁ ወደ ስምምነት ተቃርቧል። አሁንም ግን የሚቀር ሥራ አለ" ብለዋል።

"የሦስቱ አገራት መሪዎችም ሆኑ አሜሪካ፤ የሁሉንም አገራት ፍላጎት ያማከል ስምምነት እንዲደረስ ነው ጥረት ሲደረግ የቆየው። ብዙ ሥራ ይቀረናል፤ በቀጣዩ ወር ግን እንደሚጠናቀቅ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።

ምርጫ

"የአብይ አስተዳደር ተጠያቂ እና ሁሉን አሳታፊ በሆነ የዲሞክራሲ ሥርዓት ያምናል፤ አሜሪካም እንዲሁ" ያሉት የቀድሞ የሲአይኤ አለቃ ማይክ ፖምፔዮ፤ ስለቀጣዩ ምርጫ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል።

ቀጣዩ ምርጫ ነጻ እና ታዓማኒነት ያለው ሆኖ ሁሉንም እንደሚያሳትፍ ተወያይተናል ብለዋል።

አንበጣ መንጋን መከላከል

በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተውን አንበጣ መንጋ ለመከላከል አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል። በኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል አሜሪካ የ8 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንደምታደረግ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ለውጥ

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉት የለውጥ ሥራዎች ሕዝቡን በረዥም ጊዜ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ያሉት ፖምፔዮ፤ "በእዚህ ላይ የእኛ አስተዋጽኦ በተቻለን መጠን መደገፍ ነው" ብለዋል።

"እንዲህ ዓይነት ትልልቅ ለውጦች ሲካሄዱ ውጤቶች በፍጥነት ላይታዩ ይችላሉ" ያሉት ፖምፔዮ፤ በአፍሪካ መዲና ከሴት ርዕሰ ብሔር ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው እንዳስደነቃቸው አልሸሸጉም።