ዝቅተኛ ክህሎት ላለቸው ቪዛ እንደማይሰጥ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አስታወቀ

አስተናጋጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዝቅተኛ ክህሎት ባላቸውና ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ በማይጠይቁ ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦች ቪዛ እንደማይሰጥ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አስታውቋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከአውሮፓ መውጣቷን (ብሬግዚት) ተከትሎ ዝቀተኛ ክህሎት በሚጠይቁ ሥራዎች ለተሰማሩ ግለሰቦች (በእንግሊዝኛው Low-skilled workers የሚባሉት) ቪዛ እንደማይሰጥ መንግሥት ገልጿል።

አሠሪዎች አነስተኛ ክፍያ ከሚሰጥባቸው የሥራ ዘርፎች ይልቅ በቴክኖሎጂ የሚታገዙ ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩም ተጠቁሟል።

ከአውሮፓ አገራት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚደረግ ነፃ ዝውውር እአአ ታህሳስ 31 ከቆመ በኋላ፤ ከአውሮፓ ሕብረት አገራት እንዲሁም ከሌሎች አገራትም ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚያቀኑ ሰዎች እኩል እድል እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ኃላፊ ፕሪቲ ፓታል "ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ይመጣሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

ስደትን ለመግታት እቅድ የነደፈው የአገሪቱ መንግሥት፤ ስደተኞችን በተለያየ መስፈርት እየመዘኑ የመቀበል አሠራርን የመዘርጋት ውጥን አንግቧል።

ስደተኞች ከሚመዘኑበት መስፈርት አንዱ እንግሊዘኛ መቻል ሲሆን፤ ሙያዊ አበርክቷቸውም ከግምት ይገባል ተብሏል።

መስፈርቱን የሚያሟሉ ሰዎች 50 ነጥብ የሚሰጣቸው ሲሆን፤ አንድ ስደተኛ ሥራ ለመያዝ 70 ነጥብ ያስፈልገዋል። ግለሰቡን የሚቀጥረው ተቋም የሚከፍለው የደመወዝ መጠንም ከግምት ውስጥ የሚገባ ይሆናል።

ዝቅተኛ ክፍያ ባላቸውና ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ በማይጠይቁ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ስደተኞች ግን በዚህ አሠራር እንደማይካተቱ ተገልጿል።

በሌላ በኩል በግብርና ዘርፍ ወደ 10,000 የሚጠጉ ሰዎች እንዲሁም በየዓመቱ 20,000 ገደማ ወጣቶች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዲሄዱ ይመቻቻል ተብሏል።

በእርግጥ ከተለያዩ አገራት ሠራተኞች የሚቀጥሩ ድርጅቶች ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። የንግድ ተቋሞችን የሚወክል አንድ ቡድን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ካሮላይን ፌርብሬን ከነዚህ አንዱ ናቸው።

በሌላ በኩል ዝቅተኛ ተከፋዮችን ከጨዋታ ውጪ የሚያደርግ አሠራር "ኃላፊነት የጎደለው ነው" ሲሉ የገለጹት ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም የቤት ለቤት እንክብካቤ አገልግሎት ማኅበር (ሆምኬር አሶሴሽን) ቃል አቀባይ ናቸው።

የአርሶ አደሮች ማኅበር ፕሬዘዳንት ሚኒቴ ባተርስ መንግሥት ያወጣው እቅድ እንደሚያሰጋቸው ገልጸዋል።

ከአውሮፓ ሕብረት ውጪ ካሉ አገራት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለሚያቀኑ ሰዎች ቀድሞ ከነበረው አሠራር የሚቀል እንደሆነና በተቃራኒው ለአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ዜጎች መልካም ዜና እንዳልሆነ ተገልጿል።

ትምህርትና ልምድ በሚጠይቅ ዘርፍ የሚሰማሩ ስደተኞች ከሚቀጥራቸው ድርጅት ደብዳቤ ካፋፉና 70 ነጥብ ካገኙ መሥራት ይፈቀድላቸዋል። ይህ በመስተንግዶ፣ በቤት ለቤት እንክብካቤና መሰል ዘርፎች የሚሰማሩ ሰዎችን አያካትትም።

በአዲሱ እቅድ መሰረት ሁሉም ስደተኞች ከመንግሥት ገቢን የተመረኮዘ ጥቅማ ጥቅም የሚያገኙት የመኖሪያ ፍቃድ ካገኙ (የአምስት ዓመት ቆይታን ተከትሎ) ነው።

የስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው 'ማይግሬሽን አድቫይዘሪ ኮሚቴ' ባቀረበው ሀሳብ ትምህርትና ልምድ በሚጠይቅ ሥራ ላይ ለመሰማራት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የሚሄዱ ግለሰቦች የደመወዝ ጣሪያ ከ30,000 ፓውንድ ወደ 25,600 ዝቅ ይላል።

በተጨማሪም በርካታ ሠራተኛ በሌለበት ዘርፍ የሚቀጠሩ በቂ ነጥብ ሳይኖራቸው ቢያመለክቱም፤ በተለየ ሁኔታ እድል እንዲሰጣቸው የሚያስችል አሠራር በእቅዱ መካተቱ ተመልክቷል። አሁን ላይ በቂ ሙያተኛ የለም ተብለው ከተለዩት ዘርፎች መካከል ሲቪል ምህንድስና፣ ሥነ ልቦና እና ባሌት ዳንስ ይጠቀሳሉ።

በአዲሱ እቅድ ትምህርትና ልምድ በሚጠይቁ ዘርፎች የሚሰማሩ ስደተኞች ቁጥር አይገደብም። እነዚህ ከፍተኛ የሚባል ትምህርት የሚጠይቁ ዘርፎች (በእንግሊዘኛ skilled occupations የሚባሉት) የሚያካትቷቸው የሙያ መስኮች እንደሚሰፉ ተጠቁሟል።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ መማር የሚፈልጉ፤ የትምህርት እድል ማግኘታቸውን፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደሚናገሩና ራሳቸውን መደገፍ እንደሚችሉ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።

የቀድሞውን አሠራር የሚቀይረው ይህ አዲስ እቅድ የሚተገበረው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታ ካገኘ በኋላ ነው።