ከመንግሥት 550 ሚሊዮን ብር መዝብራ የተሰወረችው ዴንማርካዊት ተፈረደባት

አምስት መቶ አምሳ ሚሊዮን የመንግሥት ብር ሰርቃ የተሰወረችው ዴንማርካዊት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከመንግሥት አምስት መቶ አምሳ ሚሊዮን ብር መዝብራ የተሰወረችው ዴንማርካዊት ከሰሞኑ ክስ ተመስርቶባታል።

በመንግሥት ማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ድርጅት ውስጥ ለአርባ ዓመታት የሠራችው ብሪታ ኔልሰን አቅማቸው ለደከሙ ግለሰቦች የገንዘብ እርዳታን የሚለግስን ተቋም ገንዘብ ትቆጣጠር እንደነበር ተገልጿል።

ከሁለት ዓመታት በፊት በተደረገ ምርመራ ግን ገንዘቡን ኪሷን ለማደለብ ተጠቅማበታለች ተብሏል። የዴንማርክ ፍርድ ቤትም የስድስት ዓመት ተኩል እስር ከሰሞኑ ፈርዶባታል።

በዝቅተኛ ሙስናና መንግሥት ሁሉን ነገር ግልፅ በሆነ አሠራር በዓለም አቀፉ መድረክ ተምሳሌት በሆነችው ዴንማርክ ይህ የተለመደ ነገር አይደለም።

ብሪታ ኔልሰን ውንጀላዎቹ በቀረቡባት ወቅት ደቡብ አፍሪካ ተሰውራ ነበር። ወደ ዴንማርክ ለመመለስ የወሰነችው ዓለም አቀፉ የወንጀል አጣሪና አዳኝ ኢንተርፖል የእስር ትዕዛዝ ካወጣባት በኋላ ነው።

ለሃያ አምስት ዓመታትም ድርጅቱን በመመዝበርም ተወንጅላለች።

ብሪታ ኔልሰን 'ሶሻልስትይሬልሰን' በሚባለው ብሄራዊ የጤናና ደህንነት ላይ የሚሠራው መንግሥታዊ ድርጅት ውስጥ ነው የሰራችው።

የዴንማርክ መስማት የተሳናቸው ማኅበርን ጨምሮ ሌሎች የአካል ጉዳተኞችም በጀት የሚመደብላቸው ከዚህ ድርጅት ነበር፤ ገንዘብ መመደብም የሷ ኃላፊነት ነበር ተብሏል።

ከሦስት ዓመታት በፊት በድርጅቱ ውስጥ ላደረገችው አስተዋፅኦ የብር ሜዳልያ ሽልማትም ተሸልማለች።

ኖርዲክ ሌበር ጆርናል፤ ብሪታ ኔልሰን ለመመዝበር ያመቻት ምንም አይነት የተጠያቂነት መዋቅር ስላልነበረው ነው በማለት ፍርድ ቤቱ ላይ መከራከሪያ ሃሳብ አቅርቧል።

የ65 አመቷ ብሪታ ኔልሰን በበኩሏ "ብሩን አካውንቴ ውስጥ መጨመር ቀላል ነበር፤ ከዚያም ወደ ባሃማስ ለመዝናናት መሄድ" ብላለች።