ከ33 ዓመት በፊት የተዘረፈው ዘውድ ለጨለቆት ሥላሴ ቤተክርስቲያን እንደሚመለስ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, PM Office facebook page
ለ21 ዓመታት በኔዘርላንድስ አቶ ሲራክ አስፋው በተባሉ ግለሰብ እጅ የቆየው ጥንታዊ ዘውድ ዛሬ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ. ም. ለኢትዮጵያ ተመልሷል።
በ18ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሰራ የሚነገርለት ዘውድ፤ በኔዘርላንድስ ኤምባሲ በኩል ለኢትዮጵያ የተመለሰ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ቅርሱን ተረክበዋል።
ከመቐለ 16 ኪሎ ሜትር በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ከሚገኘውና ረዥም ዕድሜ ካስቆጠረው ሥላሴ ጨለቆት ቤተ ክርስትያን እንደተሰረቀም ይታመናል።
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ፍስሐ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ዘውዱ ለተወሰነ ጊዜ በብሔራዊ ሙዝየም ቆይቶ ለጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ይሰጣል።
"የተሰረቀው ከጨለቆት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ነበር። የሚመለስበትን ቀን ገና ባንወስንም በአድዋ በዓል ላይ ለማስረከብ አስበናል" ሲሉ ገልጸዋል።
ቅርሱ ነሀሴ 26፣ 1979 ዓ. ም. እንደተሰረቀ የሚናገሩት ዶ/ር ሙሉጌታ፤ ከቅርሱ ዝርፊያ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች ቢኖሩም፤ ቅርሱ በምን መንገድ ከአገር እንደወጣ እስካሁን አልታወቀም ብለዋል።
ቅርሱን ለ21 ዓመት በቤታቸው ያቆዩት አቶ ሲራክ ስለ ዘውዱ ለኔዘርላንድስ መንግሥት ካሳወቁ በኋላ ጉዳዩ በውጪ ጉዳይ ሚንስትር በኩል ወደ ባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ከዛም ወደ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን መመራቱን ዶ/ር ሙሉጌታ ገልጸዋል።
"ቅርሱ የጨለቆት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን በፎቶ ማስረጃዎች ካረጋገጥን በኋላ እንዲመለስ ተወስኗል" ሲሉ አስረድተዋል።
የትግራይ ክልል ቅርሱ ከተሰረቀ በኋላ ለማስመለስ ደብዳቤዎች ይጻጻፍ እንደነበር እንዲሁም ቅርሱ ከመዘረፉ በፊት የነበረበትን ሁኔታ የሚያሳዩ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች እንዳሉም አክለዋል።
"ጠቅላይ ሚንስትሩ የዳያስፖራው ምሳሌ ነህ አሉኝ"
ላለፉት 41 ዓመታት ኔዘርላንድስ ውስጥ የኖሩትና የአገሪቱን ዜግነት ያገኙት አቶ ሲራክ፤ ቅርሱን ለ21 ዓመታት ደብቀው ማቆየታቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ "ለቅርሱ ደህንነት እምነት የምጥልበት ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ በአጭር ጊዜ ይመጣል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር" ማለታቸው የሚታወስ ነው።
አሁን ባለው አስተዳደር እምነት በመጣላቸው ቅርሱን ለኢትዮጵያ ለማስረከብ መወሰናቸውን በወቅቱ ገልጸው ነበር።
አቶ ሲራክ፤ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት እስኪያገኝ የስደተኞቹን ቁሳ ቁስ ተረክበው ቤታቸው በአደራ ያስቀምጡ ነበር። ቤታቸው ይመላለሱ ከነበሩ ሰዎች አንዱ፤ ቅርሱን እሳቸው ቤት ትተውት እንደሄዱም ተናግረዋል።
አቶ ሲራክ ቅርሱን ለጠቅላይ ሚንስትሩ ካስረከቡ በኋላ ከቢቢሲ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉ ሲሆን ደስታቸውንም ገልፀዋል።
"ዛሬ የተሰማኝን ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል፤ በሕይወት እያለሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መጠቶ ዘውዱን ለኢትዮጵያ አስረክባለሁ ብዬ አልሜ አላውቅም ነበር" ብለዋል።
ለጠቅላይ ሚንስትሩ ዘውዱን ማስረከብ "ለኔ ታላቅ ክብር ነው" ያሉት አቶ ሲራክ፤ "ከ20 ዓመታት በላይ ይዤ የከረምኩትን ሸክም ከጀርባዬ አውርደውልኛል" በማለት ስሜታቸውን ገልጸዋል።
ዘውዱን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በአደራና በጥንቃቄ አስቀምጠው በማስረከባበቸውም ጠቅላይ ሚንስትሩ "የዳያስፖራው ምሳሌ ነህ" እንዳሏቸው ተናግረዋል።
ከቀደመው ትውልድ የተሸጋገረን ቅርስ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ እንዳስደሰታቸውም አክለዋል።
"ዘውዱን ለ21 ዓመታት ቤቴ ውስጥ አይቼዋለሁ። ዛሬ ቤተ መንግሥት ውስጥ ሳየው ግን ልዩና ገናና ሆኖ ታየኝ" ሲሉም አቶ ሲራክ ተናግረዋል።
የፎቶው ባለመብት, Pm Abyi Ahmed office
የዘውዱ ታሪካዊ ዳራ
በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር ከ1745-1865 በወቅቱ የእንደርታ ዙሪያ የሚባለውን ሰፊ ግዛት ያስተዳደሩት ራስ ወልደሥላሴ በአራት ቦታዎች ማለትም በጨለቆት፣ በአንጣሎ፣ በፈለግዳሮና በመቐለ ቤተ መንግሥቶችን ገንብተው ነበር። በአንድ ወቅትም ጨለቆትን ዋና ከተማቸው አድርገዋታል።
ለአሥራ ስድስት ዓመታት መንነው በቤተ ክርስቲያኗ የሚኖሩት የ82 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አባ ገብረሥላሴ፤ ሦስት ዘውዶችን ራስ ወልደሥላሴ ለቤተ ክርስቲያኗ መስጠታቸውን ለቢቢሲ መግለፃቸው የሚታወስ ነው።
ራስ ወልደሥላሴ ካበረከቷቸው ዘውዶች መካከል በኔዘርላንድስ ተገኝቶ ዛሬ ለኢትዮጵያ የተመለሰው ዘውድ አንዱ ነው።
ዘውዱን አንዳንዶች በላሊበላ እንዲሁም በፋሲለደስ ወቅት የነበረ ነው ቢሉም፤ ኒው ዮርክ ታይምስ ያናገራቸው በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ከፍተኛ ጥናት ያደረጉት ጃኮፖ ጊንስቺ፤ ዘውዱ ከሥላሴ ጨለቆት ቤተ ክርስቲያን የተሰረቀ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ጃኮፓ እንደሚሉት፤ ዘውዱ ከመጥፋቱ በፊት በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ አንድ የቤተ ክርስቲያን ቄስ ዘውዱን ራሳቸው ላይ ጭነው ፎቶ ተነስተዋል።
ዘውዱ በአይነቱ የተለየ እንደሆነ የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ዋጋውንም 55 ሺህ ዶላር ወይም 1.76 ሚሊዮን ብር ይገመታል ብለዋል።
በተለያዩ ዘመናት የኢትዮጵያ ቅርሶች ተዘርፈው ከአገር ወጥተዋል። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ከተለያዩ አገሮች ጋር ስምምነት በማድረግ ቅርሶችን ለማስመለስ ቢሠራም፤ ቅርሶች እንዳይዘረፉ መከላከል ጉልህ ቦታ እንደሚሰጠው የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ተናግረዋል።
"ቅርስ ህልውና ነው፤ ለዘመናት የሰው ልጅ ያለፈበትን ታሪክና ባህል የሚገልጽ ቅርስ እኛነታችንን ይገልጻል" የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ቅርሶች ከማንነት መገለጫነታቸው ባሻገር የቱሪስት መስህብ እንደሆኑ በማከልም ማኅበረሰቡ ቅርሶቹን መጠበቅ እንዳለበት ገልጸዋል።