በናይሮቢ በፖሊስ የተገደለው ሞተረኛ ጉዳይ ከባድ ተቃውሞ አስነሳ

ሞተርሳይክል

የፎቶው ባለመብት, AFP

በመቶዎች የሚቆጠሩ በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኙ ሞተረኞች ሆስፒታል ውስጥ አንድ ሞተረኛ መገደሉን ተከትሎ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል። ሞተረኛው አንድ ህጻንን ለመርዳት ድንገተኛ ክፍል ሲገባ በፖሊስ እንደተገደለ እየተዘገበ ነው።

የ 24 ዓመቱ ዳንኤል ምቡሩ ውሀ ውስጥ ሰምጦ በህይወትና ሞት መካከል የነበረን አንድ ህጻን ሕይወት ለማዳን ነበር ሞተሩን እየነዳ ወደ ድንገተኛ ክፍል ዘው ብሎ የገባው።

ነገር ግን የሆስፒታሉ ጠባቂዎች እንዴት ከነሞተርህ ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ትገባለህ በማለት ሊያስቆሙት ሲሞክሩ ግርግር ይፈጠራል። እሰጥ አገባው ለትንሽ ደቂቃዎች ከቆየ በኋላ የሆስፒታሉ ሰራተኞች ፖሊስ ይጠራሉ።

በዚሁ ግርግር በሀል ሞተረኛው በፖሊስ ተተኩሶበት እንደሞተ ሌሎች ሞተረኞች ገልጸዋል። ምንም እንኳን ፖሊስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠብም የኬንያ ተሟጋቾች ግን ፈጣን ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በኬንያ በተለይም በመዲናዋ ናይሮቢ 'ቦዳቦዳ' በመባል የሚታወቁት ሞተረኞች በከፍተኛ ሁኔታ የትራንስፖርት ፍሰቱን የሚያግዙ ናቸው።

''ወጣቱ ሞተረኛ ህፃኑን ለማዳን የቻለውን ሁሉ ነው ያደረገው። ሊመሰገን የሚገባው ዜጋ ነው። እሱ ያሰበው ወደ ድንገተኛ ክፍል ሄዶ ህጻኑን ስለማዳን ብቻ ነበር'' ብለዋል የብሄራዊ 'ቦዳቦዳ' ደህንነት ማህበር ዋና ጸሀፊው ኬቨን ሙባዲ።

አክለውም የማህበሩ አባላትና ማንኛውም ሞተረኞች እንዲረጋጉና ፖሊስ ገለልተኛ በሆነ መልኩ አፋጣኝ ምርመራ እንዲጀመር አሳስበዋል።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኬንያ ቅርንጫፍም በበኩሉ ምርምራ እንዲካሄድ የጠየቀ ሲሆን ሞተረኛው ድብደባ ከተፈጸመበት በኋላ ወደ ሆስፒታሉ የጥበቃ ቢሮ ከተወሰደ በኋላ በፖሊስ ተተኩሶበት ሕይወቱ አልፋለች ብሏል።

በርካታ ኬንያውያን በማህበራዊ ሚዲያዎች በኩል ዳንኤል ምቡሩን ተኩሶ የገደለው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ስር ውሎ ለፍርድ እንዲቀርብ ቢጠይቁም ፖሊስ እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ሞተረኛው ተሸክሞት ወደሆስፒታል የመጣው ህጻን ህክምናውን እየተከታተለ እንደሆነና በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን ''ዳንኤል ምቡሩ ጀግናችን ነው፤ ሞት አይገባውም ነበር'' ብለዋል ኬንያውያን።