ዘረኛ የተባለውን የፋሽን ትዕይንት ያዘጋጀው ይቅርታ ጠየቀ

ሞዴል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መቀመጫውን በአሜሪካዋ ኒው ዮርክ ያደረገ አንድ የፋሽን ትምህርት ቤት ያዘጋጀው የፋሽን ትዕይንት ዘረኝነትን አስተጋብቷል መባሉን ተከትሎ ይቅርጣ ጠየቀ።

በፋሽን ትዕይንቱ የተሳተፉ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ትልልቅ ጆሮዎችና ከንፈሮች እንዲሁም ጥቅጥቅ ያለ አርቲፊሻል ሽፋሽፍት እንዲለብሱ የተደረገ ሲሆን ዝንጀሮዎችን እንዲመስሉ ተደርገዋል በሚል ነው ወቀሳ የደረሰባቸው።

የፋሽን ትዕይንቱን በመጀመሪያ የተቃወመችው አንዲት ጥቁር አሜሪካዊት ሞዴል ናት። ''በግልጽ ዘረኝነት ነው የተፈጸመው'' ብላለች።

'ዘ ፋሽን ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ' በመባል የሚታወቀው ትምህርት ቤት ጉዳዩን እየመረመርኩት ነው ብሏል።

''በአሁኑ ሰዓት ባለን መረጃ ለፋሽን ትዕይንቱ ጥቅም ላይ የዋሉት ተጨማሪ አርቲፊሻል አካላት ለየት ባለ መልኩ አልባሳቱን ለማቅረብ የተዘጋጁ እንጂ ከዘረኝነት ጋር የተያያዘ ምንም ነገር አላገኘንም'' ብለዋል ትምህርት ቤቱ ፕሬዝዳንት ጆይስ ኤፍ ብራውን።

አክለው ግን ''እኛ ማስተላለፍ የፈለግነው መልዕክት በሌላ መልኩ መተርጎሙን አስተውለናል። ለዚህም ለሰራነው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን ። በዝግጅቱ ለተሳተፉ ሞዴሎች፣ ተማሪዎች እና በሁኔታው ለተበሳጩ ሰዎች በሙሉ ይቅርታ ለመጠየቅ እንወዳለን'' ብለዋል።

'ዘረኛ' የተባለው የፋሽን ትዕይንት ወደ መገናኛ ብዙኃን ጆሮ የደረሰው በዝግጅቱ አልሳተፍም ብላ ተቃውሞዋን በይፋ በገለጸች ጥቁር ሞዴል አማካኝነት እንደሆነ ታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጥቁር አሜሪካዊቷ ሞዴል ኤሚ ሌፍር ለኒውዮርክ ፖስት እንደገለጸችው ለፋሽን ትዕይንቱ አዘጋጆች በውሳኔያቸው ደስተኛ እንዳልሆነችና ሌላ መልዕክት ሊያስተላልፍ እንደሚችል ነግሬያቸው ነበር ብላለች።

''ልብሶቹን ለመልበስ አልፈልግም፤ ጥሩ ስሜት አይሰማኝም ስላቸው 'ለ 45 ሰኮንዶች ብቻ ነው፤ ጥሩ ስሜት ባይሰማሽም ችግር የለውም' አሉኝ'' ብላለች።