ቻይና ዘረኝነት ተንፀባርቆበታል ባለችው ፅሁፍ ምክንያት የዋልስትሪት ጋዜጠኞችን ከሃገሯ አባረረች

የዋል ስትሪት ጆርናል ጋዜጠኞች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አምስት ቀናት ተሰጥቷቸዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ዘረኝነት ተንፀባርቆበታል ባለችው ፅሁፍ ምክንያት ሶስት የዎል ስትሪት ጋዜጠኞች ከሃገሯ እንዲወጡ አዘዘች።

ከሁለት ሳምንት በፊት የታተመው ይህ ፅሁፍ አገሪቷ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እያደረገችው ያለውን ጥረት "በአስነዋሪ ሁኔታ" ተችቷል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተደጋጋሚ ጋዜጣው ይቅርታ እንዲጠይቅ ቢጠይቁም ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል።

ዎልስትሪት ጋዜጣ እንዳሳወቀው ፅሁፉን የፃፉት ጋዜጠኞች ቻይናን ለቀው እንዲወጡ አምስት ቀናት ተሰጥቷቸዋል።

በዎል ስትሪት ጆርናል ላይ የወጣው ፅሁፍ ላይ የቻይና ባለስልጣናት ለኮሮና ቫይረስ የሰጡትን ምላሽ "ሚስጥራዊ" እና መንግሥት ራሱን ያስቀደመበት ነው በማለት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በቻይና ላይ መተማመን አጥቷል በማለት ያትታል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጌንግ ሹዋንግ እንዳሉት ፅሁፉ "ዘረኛ" እንዲሁም ቻይና የኮሮና ቫይረስን ወረረሽኝ እንዳይዛመት እያደረገች ያለችውን ጥረት ሆን ብሎ ለማቅለል ያለመ ነው ብለውታል።

ወረርሽኙ እስካሁን የ2ሺ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።

" እንዲህ አይነት የዘረኝነት ፅሁፍን የሚፅፉ እንዲሁም ሆን ብለው በተንኮል ቻይናን ለመተንኮስ የሚፈልጉ ሚዲያዎችን የቻይና ህዝብ አይፈልጋቸውም" በማለት ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን የቻይና መንግሥት ከአገር የተባረሩትን ጋዜጠኞች ስም ባይጠቅስም ዎል ስትሪት ጆርናል ሁለቱ፣ ጆስ ቺን (ምክትል ኃላፊ) እና ቻዎ ዴንግ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ሲሆን አንደኛው ደግሞ የአውስትራሊያ ዜግነት ያለው ፊሊፕ ዌን ናቸው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ የጋዜጠኞቹን መባረር አውግዘውታል።

ማይክ ፖምፔዮ ነፃ ፕሬስንም ሆነ ንግግርን ማገድ ተገቢ እንዳልሆነና የቻይና መንግሥት ስህተት ነው ብሎ ካመነ መሟገቻ ሃሳብ ማቅረብ ይገባ ነበር ብለዋል ባወጡት መግለጫ።

የጋዜጣው አሳታሚ ዊልያም ሉዊስ በበኩላቸው ባወጡት መግለጫ በውሳኔው " ከልብ እንዳዘኑና" በዜና ክፍሉና በአስተያየት ፅሁፎች መካከል ግልፅ ያለ ልዩነት ያስፈልጋል ብለዋል።

"ጋዜጣችን ላይ የተለያዩ እይታዎችን የምናስተናግድበት አስተያየት በተለያዩ ሰዎች ይፃፋሉ፤ እነዚህን እይታዎች ብዙዎች ሊስማሙማባቸው ወይም ላይስማሙባቸው ይችላሉ። ዋናው ነገር ግን እንዲህ የሚያስቀይም ነው ብለን አላሰብንም፤ ይሄ የኛም ፍላጎት አይደለም" ያሉት ሉዊስ " ነገር ግን ፅሁፉ የቻይናን ህዝብ በማበሳጨቱ የምንፀፀትበት ጉዳይ ሆኗል"

ህጋዊ ፈቃድ ያላቸው ጋዜጠኞች ከቻይና እንዲለቁ ሲወጡ ሲነገራቸው ይህ በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው እንደሆነ የቢቢሲው ጆን ሱድዎርዝ ከቤጂንግ ዘግቧል።

ጥያቄ የተነሳበት ፅሁፍ "የታመመው እስያዊ" (ዘ ሲክ ማን ኦፍ ኤዥያ) የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን በ18ኛውና 19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ቻይናን ለመግለፅ ይጠቀሙበት የነበሩ "አስነዋሪ ቀላቶች ተካተዋል ተብሏል።

እነዚህ አስፀያፊ ቃላቶች ቻይና ውስጥ ያለውን የውስጥ ክፍፍል ከዓለም ኃያላን ጋር በማወዳደር የሚገልፁ ናቸው።

እንደ ኒውዮርክ ታይምስ ከሆነ የዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጠኞች ራሳቸው ርዕሱ አስነዋሪ ስለሆነ እንዲቀየር ጎትጉተው ነበር በሚል ዘግቧል።

የውጭ ሃገራት ዘጋቢዎች ማህበር በበኩሉ ውሳኔውን ፅንፈኛና ጋዜጠኞችን ለማስፈራራት የተደረገ ነው ብለውታል።

በቅርቡ አሜሪካ በአገሯ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የቻይና መንግሥት ጋዜጠኞች ላይ ያሉ ህግጋትን ጠበቅ በማድረግ "የውጭ መልእክተኞች" በሚል መድባቸዋለች።

ዢኑዋን ጨምሮ ለቻይና ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ የሚሰሩ ሰራተኞቻቸውንም ዝርዝር እንዲሰጧቸው የጠየቀች ሲሆን፤ በሚያደርጉት ዘገባ ምንም ክልከላ የለም ተብሏል።