የሌሴቶው ጠቅላይ ሚኒስትር በሚስታቸው ግድያ ተከሰሱ

ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ

የሰማኒያ ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት የሌሴቶው ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ የቀድሞ ሚስታቸውን በመግደል ወንጀል መከሰሳቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ በመጪው ሐምሌ ወር ላይ በእድሜ መግፋት የተነሳ ከስልጣናቸው እንደሚለቁ ጠቁመዋል። ቢሆንም ግን ስለግድያው ክስ ያሉት ነገር የለም።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሁኗ ባለቤት ሜሲያህ ታባኔ ቀደም ሲል ከግድያው ጋር በተያያዘ ክስ ተምስርቶባታል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የቀረበው ክስ በደቡብ አፍሪካ ተከባ የምትገኘውን የተራራማዋን የሌሴቶን ሕዝብ ያስደነገጠ ሲሆን፤ ክሱ በደቡባዊ አፍሪካ በስልጣን ላይ እያሉ በግድያ ወንጀል የተከሰሱ የመጀመሪያው መሪ ሆነዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ከመረከባቸው ከሁለት ቀናት በፊት ነበር ግድያው የተፈጸመው ተብሏል።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ ግድያውን "ጭካኔ" ሲሉ ገልጸውት የነበረ ሲሆን አሁን ግን በግድያው ውስጥ እጃቸው አለበለት በማለት ፖሊሰ ከሷቸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ነገ አርብ ክስ እንደሚመሰረትባቸውም ተገልጿል።

ሟቿ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ሊፖሌሎ ታባኔ በዋና ከተማዋ ማሴሮ ዳርቻ ላይ ወደሚገኝ ቤታቸው ሲያቀኑ ነበር በቅርብ እርቀት በጥይት ተመትተው ተገድለው የተገኙት።

በግድያው ወቅትም ግለሰቧ ከቀድሞ ባለቤታቸው ጋር ከበድ ባለ የፍቺ ውዝግብ ውስጥ እንደነበሩም ተገልጿል። በጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከ42 ዓመቷ ሜሲያህ ጋር እንደሚስት አብረው እየኖሩ ነበር።

ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመረጡት ታባኔ ሚስት ነኝ በማለት ለፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ሟች የአገሪቱ ቀዳማዊ እመቤት መሆናቸው ተወስኖላቸው ነበር።

ነገር ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመተ በዓል ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ባልታወቀ ሁኔታ ተገድለው ተገኝተዋል። ይህንንም ተከትሎ ሁለተኛዋ ሴት በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደሚስት ተገኝታ ነበር።

ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሜሲያህ ዋና ከተማዋ ውስጥ በሚገኝ ስታዲየም ተዘጋጅቶ በርካታ ሕዝብ በታደመበት ድግስ በካቶሊክ ቤተክረስቲያን ሥርዓት ጋብቻቸውን ፈጽመዋል።

ሜሲያህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚስት ግድያ ክስ ቀርቦባት በዋስ ተለቃለች፤ እስካሁንም የቀረበባትን የወንጀል ክስ መፈጸም አለመፈጸሟን በሚመለከት ቃሏን አልሰጠችም።