ሩስያ ትራምፕን ዳግመኛ ለማስመረጥ እየሞከረች መሆኑ ተጠቆመ

ፑቲን እና ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሩስያ ትራምፕን በድጋሚ ለማስመረጥ በአሜሪካ ፖለቲካ እጇን ለማስገባት እየሞከረች መሆኑን የአገሪቱ የደህንነት ተቋም ማስጠንቀቁ ተዘገበ።

በህዳር ወር የሚካሄደውን ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሸንፉ ለማድረግ ሩስያ እየጣረች መሆኑ በምክር ቤቱ የደህንነት ኮሚቴ መገለጹን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሀን እያተቱ ይገኛሉ።

ትራምፕ በተባለው ነገር እጅግ እንደተቆጡና ዴሞክራቶች ዜናውን ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ መናገራቸውም ተገልጿል።

የኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ይህ መረጃ ይፋ በተደረገበት ስብሰባ ላይ የትራምፕን ክስ የመራው ዴሞክራት አዳም ሺፍ መገኘቱ ፕሬዘዳንቱን አበሳጭቷቸዋል።

የምክር ቤቱን የደህንነት ስብሰባ የተካፈሉት የትራምፕ ደጋፊዎች፤ ፕሬዘዳንቱ ሩስያን በተመለከተ ቆራጥ ውሳኔ ላይ እንደደረሱና በዚህ ምክንያትም ከአውሮፓ አገራት ጋር ያላቸው ወዳጅነት መጥበቁን ገልጸዋል።

አዳም ሺፍ በትዊተር ገጻቸው እንዳሉት፤ ዶናልድ ትራምፕ የውጪ አገራት በምርጫው እጃቸውን ስለማስገባታቸው በአሜሪካ የደህንነት ተቋሞች እና በምክር ቤቱ መካከል በሚደረገው የመረጃ ልውውጥ ጣልቃ ከገቡ፤ የሌሎች አገራትን ተሳትፎ ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ሊያከሽፉ ይችላሉ።

ትራምፕ ሀሙስ እለት የደህንነት ጉዳይ ጊዜያዊ ኃላፊያቸው ጆሴፍን ማጉሬን በሌላ ተክተዋል። ፕሬዘዳንቱ የደህንነት ጉዳዮች ቋሚ ኃላፊ ያደርጓቸዋል ተብለው የነበሩት ጆሴፍ በስብሰባው ላይ በመገኘታቸው ፕሬዘዳንቱ ሀሳባቸውን እንደቀየሩ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።

ከደህንነት ጉዳይ ጊዜያዊ ኃላፊነት የተነሱት ጆሴፍን፤ በጀርመን የአሜሪካ አምባሳደር በሆኑት ሪቻርድ ግሪኔል እንደሚተኩ ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል።

ሁለት የትራምፕ አመራር ውስጥ ያሉ ባለስልጣኖች በበኩላቸው ከስብሰባው በኋላ የጆሴፍ መነሳት የአጋጣሚ ጉዳይ መሆኑን ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።

የአሜሪካ የደህንት ኃላፊዎች፤ ሩስያ የትራምፕን የምረጡኝ ቅስቀሳ በማጉላት እና አጠቃላይ የምርጫ ሂደትን በማወክ በ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብታ ነበር ይላሉ።