በቡራዩው ጥቃት የአባ ቶርቤና የቀድሞ የኦነግ ወታደሮች ተጠርጥረው መያዛቸው ተገለጸ

ኮሚሽነር ሰለሞን ታደሰ

የፎቶው ባለመብት, ETV

የምስሉ መግለጫ,

ኮሚሽነር ሰለሞን ታደሰ

በቡራዮ ከተማ ትናንት በተገደሉት ኮሚሽነር ሠለሞን ታደሰ ግድያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በትናንትናው ዕለት በቡራዩ ከተማ አስተዳደር አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ሆቴል ምሳቸውን እየተመገቡ የነበሩት የከተማው ፖሊስ አዛዥ፣ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አዛዥ እንዲሁም ሌላ የፖሊስ አባልና ድምጻዊ ላይ ተኩስ ተከፍቶባቸው የነበረ ሲሆን ኮሚሽነር ሠለሞን ሲገደሉ ሌሎቹ መቁሰላቸው ይታወሳል።

በወንጀሉ የተጠረጠሩ ሰዎች የቀድሞ የኦነግ ወታደሮችና በአባ ቶርቤ (ባለሳምንት) ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ናቸው በማለት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በትናንትናው ዕለት መግለጫ አውጥቷል።

ይህንን ተከትሎም የከተማው ፖሊስና የልዩ ኃይል ፀጥታ አባላት በከተማ አስተዳደሩ አቅራቢያ የነበሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸው የተሰማ ሲሆን በወንጀሉ የተጠረጠሩ ሰዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አቶ ጌታቸው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ መረጃ እንደሌላቸው እና እስካሁን ድረስ በግድያው የተጠረጠሩ ለሕግ እንዲቀርቡ አለመለየታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው በቡራዩ ከተማ በተደጋጋሚ የተከሰቱ ግጭቶችን በማንሳትም የከተማው የፀጥታ ኃይል መስራት ያለበት በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ገልፀዋል።

በተደጋጋሚ በከተማውና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ግጭት ሲፈጠርም "አባ ቶርቤ" የሚለው ስም በጥቅሉ እንደሚጠራ በማስታወስ በደፈናው ከመግለጽ ይልቅ ይህ ቡድኑ ማን እንደሆነና ለምን ተልዕኮ እንደተሰማራ በአግባቡ ተመርምሮ ለህዝቡ መገለጽ እንደሚኖርበት አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደም ኦነግ አመራሮች አባ ቶርቤ የሚባለው ቡድን ከእነርሱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽ መናገራቸው ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት በቡራዩ በአንድ ሆቴል ምረቃ ላይ በተፈጠረ አለመግባባትና ግጭት ድምጻውያንና ታዳሚዎች ላይ ጉዳት መድረሱን መዘገባችን ይታወሳል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ጌታቸው ባልቻ የቡራዩ ከተማ አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ሠለሞን ታደሰ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት እንደሚፈፀም ጨምረው አስታውቀዋል።

በቡራዩ ትናንት የተከሰተው ምን ነበር?

የቡራዩ ከተማ አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ታደሰ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የልዩ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ተስፋዬ ድንቁ፤ እንዲሁም ኮማንደር ተስፋዬና ሌሎች ምሳ እየበሉ በነበረበት ወቅት በተከፈተባቸው ተኩስ በጥይት የተመቱ ሲሆን የአቶ ሠለሞን ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ቀሪዎቹ ግን የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።

ከፖሊስ አባላቱ በተጨማሪ ድምጻዊ ደጀኔ ካሳዬና ሌላ የመንግሥት ሠራተኛ እንደነበሩ ከኮሚዩኬሽን ቢሮ ኃላፊው ሰምተናል።

አቶ ጌታቸው እንዳሉት በአራቱ ግለሰቦች ላይ ጥቃቱ የተሰነዘረው ቡራዩ ከተማ አስተዳደር አቅራቢያ ምሳ እየተመገቡ ሳሉ ነበር።

ኮማንደር ተስፋዬን ጨምሮ በጥይት የተመቱት ሦስቱ ግለሰቦች ወደ ኮሪያ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና እርዳታ እያገኙ እንደሚገኙ አቶ ጌታቸው የተናገሩ ሲሆን፤ ግለሰቦቹ በአሁን ሰዓት በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙስጠፋ ከድር በበኩላቸው አራቱ ሰዎች ላይ የተፈፀመው "ወንጀል ጭካኔ የተሞላበት ሽብር ነው" ሲሉ ለኦቢኤን ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት ጥቃቱ የተፈፀመው ግለሰቦቹ ምሳ እየበሉ በነበሩበት ሆቴል ውስጥ ነው።

ኮሚሽነር ከድር በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ፖሊስ የምርመራ ሥራ መጀመሩን እና ውጤቱንም ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ኮሚሽነሩ ህዝቡ ደህንነቱ እንዲያረጋግጥ ከመንግሥት አካላት ጋር በንቃት አብሮ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ የፖሊስ ኮሚሽን ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ላይም በግድያው የጠረጠራቸው የኦነግ የቀድሞ ወታደሮችና አባ ቶርቤ በሚባለው ቡድን ስም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን መሆኑን አስታውቆ ነበር።