ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በአንድ ቀን ውስጥ በእጥፍ ጨመረ

አምቡላንስና የህክምና ባለሙያዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በአንድ ቀን ውስጥ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ባለስልጣናቱ እንዳሉት ከትናንት አርብ ጀምሮ ባለው መረጃ ዛሬ ቅዳሜ ብቻ 229 አዳዲስ በኮሮናቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎች ተገኝተው በተደረገው ምርምራ ቫይረሱ እንደለባቸው ተረጋግጧል። ይህም በአገሪቱ ያሉትን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 433 ከፍ አድርጎታል።

የደቡብ ኮሪያ ምክትል የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እንዳሉት የበሽታው ወረርሽኝ "አሳሳቢ የሆነ አዲስ ደረጃ ላይ ሰርሷል"።

ባለስልጣናት እንዳረጋገጡት አዲሶቹ በበሽታው ከተያዙት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በአገሪቱ ደቡብ ምሥራቅ በምትገኘው የዴጉ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታልና የሐይማኖት ስፍራ ጋር የተያያዙ ናቸው።

እስካሁን በበሽታው በደቡብ ኮሪያ ውስጥ ሁለት ሰዎች የሞቱ ሲሆን ቁጥሩም እየጨመረ ሊሄድ ይችላል የሚል ስጋት አለ።

የበሽታው ምንጭ እንደሆነ የተጠረጠረው ሆስፒታል በሚገኝበት ዴጉ አቅራቢያ ያለው ቾንግዶ የተባለው አካባቢ ልዩ ቁጥጥር የሚደረግባቸው አካባቢዎች ተብለው ተለይተዋል።

በዚህ የተነሳ በዴጉ ከተማ ያሉ ጎዳናዎችም ጭር ብለዋል።

ደቡብ ኮሪያ ከ76 ሺህ በላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎችና ከ2 ሺህ ሦስት መቶ በላይ ከሞቱባት ቻይና ቀጥሎ ከፍተኛው የተረጋገጠ የህሙማን ቁጥር ያለባት አገር ሆናለች።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክትር የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሐኖም እንዳሉት፤ አዲስ እየታየ ያለው የወረርሽኙ ስርጭት ፍጥነት እጅጉን አሳሳቢ ነው። በተለይ ደግሞ ደካማ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ባላቸው የአፍሪካ አገራት ውስጥ በሽታው ከተከሰተ የሚያስከትለው ቀውስ አሳስቧቸዋል።