ደቡብ አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ፍራቻ የእግር ኳስ ቡድኗን ወደ ጃፖን አልክም አለች

የደቡብ አፍሪካ የእግር ኳስ ቡደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ደቡብ አፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ፍራቻ የኦሎምፒክ እግር ኳስ ቡድኗን ወደ ጃፓን አልክም ማለቷ ተዘግቧል። ደቡብ አፍሪካና ጃፓን ከአራት ወራት በኋላ የሚካሄደው የቶክዮ ኦሎምፒክስ ከመድረሱ በፊት የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ እቅድ ይዘው ነበር።

ጨዋታው የታሰበው ከአንድ ወር በኋላ ቢሆንም ደቡብ አፍሪካ ባላት ስጋት ምክንያት ተሰርዟል።

በጃፓን እስካሁን ባለው 85 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሲሆን አንድ ሰው መሞቱን ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ማህበር ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ ጌይ ሞኮየና እንዳሉት የጃፓን እግር ኳስ ማህበር ውሳኔያቸውን ቀስ ብለው እንዲያጤኑት ቢነግራቸውም ውሳኔያቸውን እንደማይቀለብሱት አሳውቀዋል።

"ጃፓን ውሳኔያችሁን ቀይሩ እያለችን ነው፤ እኛ ግን ምንም የምንቀይርበት ሁኔታ የለም። ለኛ ቅድሚያ የምንሰጠው የተጨዋቾቻችን ደህንነት ነው" ያሉት ጌይ ሞኬና አክለውም " የተጨዋቾቻችንን ህይወት አደጋ ውስጥ መክተት አንፈልግም፤ በየቀኑ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ነው፤ እንዲህ አይነት ስጋትን የመሸከም አቅሙ የለንም" ብለዋል።

የአይቮሪ ኮስትም ቡድን ከወር በኋላ ለወዳጅነት ጨዋታ ወደ ጃፓን ለማምራት እቅድ የተያዘ ሲሆን እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም።

በሐምሌ ወር ለሚጀምረው ኦሎምፒክ ስድስት ከተሞች የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ለማሰተናገድ ተመርጠዋል። ደቡብ አፍሪካና አይቮሪ ኮስት በወንዶች እግርኳስ ለመሳተፍ ከአፍሪካ ማጣሪያውን አልፈዋል።

የመጪው ኦሎምፒክ ስራ አስፈፃሚ ቶሺሮ ሙቶ ከዚህ ቀደም እንዳሉት የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን መሰረዝም ሆነ ማስተላለፍ ግምት ውስጥ አለመግባቱን ነው።