በርኒ ሳንደርስ የዴሞክራት ፖርቲ እጩ መሆናቸው እየተጠቆመ ነው

በርኒ ሳንደርስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የግራ ፖለቲካ አራማጁ በርኒ ሳንደርስ በሚቀጥለው የአሜሪካ ምርጫ ዴሞክራቶችን ወክለው ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር እንደሚፋለሙ እየተጠቆመ ነው።

ይህም ሁኔታ የኔቫዳ ካውከስ ምርጫን ማሸነፋቸውን ተክትሎ ነው በርኒ ሳንደርስ ቀጣዩ የዴሞክራት እጩ መሆናቸው የተነገረው።

ምንም እንኳን ዲሞክራቶችን ወክሎ እጩ የሚሆነው እስከሚታወቅ ድረስ ፉክክሩ ያላለቀ ነው ቢባልም የኔቫዳ ውጤታቸው ግን መሪ ቦታ ላይ አስቀምጧቸዋል እየተባለ ነው።

ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ከሌሎች ሁለት ግዛቶች በተሻለ የኔቫዳ ውጤታቸው የተሻለ ነው ተብሏል። ጆ ባይደን በአይዋና ኒው ሃምፕሻየር ያገኙት ድምፅ ከጠበቁት በታች ነው ተብሏል።

በነዚህ ግዛቶች የአራት ወሩ የተፎካካሪዎች ምርጫ ክፍት የሆነ ሲሆን፤ ተወዳዳሪዎችም ትራምፕን ለመፋለም ብቁ መሆናቸውን መራጮችን ሊያሳምኑ ይገባል።

የኔቫዳ ቆጠራ እስካሁን ያላለቀ ሲሆን፤ በተደረገው 50% ቆጠራ የግራ ፖለቲካ አራማጁ የቬርሞንቱ ሴናተር በርኒ ሳንደርስ 47% % ድምፅ በማግኘት የመሪነት ቦታውን የተቆናጠጡ ሲሆን፤ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን 19% በማግኘት በሁለተኛ ደረጃ ይከተላሉ።

ሌላው ድምፅ በሌሎች ተወዳዳሪዎች የተከፋፈለ ሲሆን ፒት ቡትጂየግ 15% እንዲሁም ኤልዛቤት ዋረን 10% ድምፅ አግኝተዋል።

ከአስራ አምስት በመቶ በላይ ድምፅ ያገኙ ተወዳዳሪዎች ልዑካን የማግኘት እድል የሚሰጣቸው ሲሆን ሲሆን፤ እነዚህ ልዑካን በመቀጠልም ፓርቲው በሐምሌው ወር በሚያደርገው ጉባኤ ለእጩዎቻቸው ድጋፍ የሚሰጡ ይሆናል።

ከባለፈው ቅዳሜ በፊት በርኒ ሳንደርስ 21 ልዑካን የነበራቸው ሲሆን ዴሞክራት ፓርቲን ወክለውም ለመወዳደር የሚያስፈልጋቸው 1990 ልዑካኖች ናቸው።

ከአሁኑ የኔቫዳ ድላቸው በኋላ የልዑካን ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምር ሲሆን ለእጩነት የሚያደርሳቸውንም ቁጥር ያገኛሉ ተብሏል።

በአይዋ የነበረው ምርጫ በአዲስ መተግበሪያ ምክንያት የቴክኒክ ችግር ገጥሞ የነበረ ሲሆን፤ ይህ መተግበሪያን በኔቫዳ ያልተጠቀሙ ቢሆንም በጎ ፈቃደኞች ውጤት መመዝገቢያው ስልክ ጋር ለመገናኘት ችግር ገጥሟቸው ነበርም ተብሏል።

ቅዳሜ ምሽት ድላቸውን አስመልክተው በርኒ ሳንደርስ ባደረጉት ንግግር ከተለያየ ትውልድ እንዲሁም ህዝብ የተዋቀሩትን ደጋፊዎቻቸውን አመስግነው ትራምፕን ወርፈዋቸዋል። " አሜሪካውያን በአንተ ምክንያት ህመም ላይ ናቸው፤ ሁልጊዜ በሚዋሽ ፕሬዚዳንት ምክንያት ተዳክመዋል" በማለት በርኒ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው በትዊተር ገፃቸው ላይ በበርኒ ሳንደርስ ማሸነፍ ምስጋናቸውን ቢያስተላልፉም "እብዱ በርኒ" ብለውታል።