ከአትሌቲክስ የታገደው አሠልጣኝና የሞ ፋራህ ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ ወድቋል

ሞ ፋራህ አበራታች መድኃኒት ተጠቅሞ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአትሌቲክስ ዓለም የታገደው አሠልጣኝ አልቤርቶ ሳላዛር እና እንግሊዛዊው ሯጭ ሞ ፋራህ ያላቸው ግንኙነት ጥያቄ ጭሯል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሞ ፋራህ፤ ከለንደን ማራቶን በፊት ኤል-ካርኒታይን (L-carnitine) የተሰኘ መድኃኒት አልወሰድኩም ሲል ለአሜሪካው ፀረ-አበራታች መድኃኒት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ተናግሯል።

በኋላ ላይ ግን መውሰድ አለመውሰዴን አላስታውስም ሲል ምላሹን ቀይሮ ተናግሯል።

የቢቢሲው ፓኖራማ ፕሮግራም እንዳራጋገጠው የዩናይትድ ኪንግደም አትሌቲክስ ባለሥልጣናት ሞ ፋራህ የወሰደው መድኃኒት ተገቢ ይሆን አይሆን የሚል ስጋት አድሮባቸው ነበር።

ስዊትዘርላንዳዊው ሳላዛር፤ ናይኪ ኦሬጎን ፕሮጀክት በተሰኘ ስም ከሞ ፋራህ ጋር ከ2011-17 ድረስ ሠርቷል። ነገር ግን 2015 ላይ ሞ ፋራህን ለዚህ ደረጃ አብቅቷል ተብሎ የሚነገርለት ሳላዛር ስሙ በክፉ ይነሳ ጀመር።

ግለሰቡ ምንም እንኳ ሳላዛር የቀረበበትን ክስ ተቃውሞ ይግባኝ ቢጠይቅም፤ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ሕግ ተላልፏል ተብሎ በዓለም አትሌቲክስ የአራት ዓመት ዕግድ ተጣለበት።

ሳላዘር ከቀረበበት ክስ መካከል አንዱ ኤል-ካርኒታይን የተሰኘውን የተፈቀደ መድኃኒት ከሌሎች መድኃኒቶች ጋር ቀላቅሎ ባልተገባ መንገድ ተጠቅሟል የሚል ነው።

አሚኖ አሲድ ያዘለው ኤል-ካርኒታይን የተሰኘው ይህ መድኃኒት ለአትሌቶች ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። የዓለም ፀረ-አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ መድኃኒቱን ከ50 ሚሊ ሊትር ባልበለጠ በ6 ሰዓታት ልዩነት ውስጥ እንዲወሰድ ይመክራል።

2014 ላይ በተካሄደው የለንደን ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው ሞ ፋራህ ስምንተኛ ወጣ። ከሦስት ዓመታት በኋላ አንድ ጋዜጣ በወቅቱ ሞ መድኃኒት ተጠቅሟል ሲል ዘገበ።

በወቅቱ ሞ ፋራህ የወሰደው መድኃኒት መጠን 13.5 ሚሊ ሊትር እንደሆነና ከዩኬ አትሌቲክስ ባለሥልጣናት ጋር በተደረገ ምክክር እንደሆነም ተገነረ። ሕግ መጣሱን የሚያመላክት መረጃ ግን ሊገኝ አልቻለም።

አዲሱ መረጃ. . .

ቢቢሲ ፓኖራማ አዲስ ያገኘው መረጃ ሳላዛር በሞ ፋራህ ላይ የነበረውን ተፅዕኖ የሚያሳይ ነው። የዩኬ አትሌቲክስ ሰዎች በወቅቱ በመድኃኒቱ ጉዳይ ስጋት እንዳደረባቸው የሚያሳይ ኢሜይል ቢቢሲ ፓኖራማ አግኝቷል።

በኢሜይሉ ምልልስ ላይ የአትሌቲክስ ባለሥልጣናት ሞ ፋራህ መድኃኒቱን መውሰዱ ተገቢ ነው አይደለም በሚለው ጉዳይ ላይ ሐሳብ ተለዋውጠዋል። በስተመጨረሻም አትሌቱ መድኃኒቱን እንዲወስደ ይሁንታ ተሰጠ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ነገር ግን የተፈለገው ዓይነት የኤል-ካርኒታይን ንጥረ-ነገር እንግሊዝ ውስጥ ሊገኝ አልቻለም። ነገር ግን መላ የማያጣው ሳላዛር ከየትም ከየትም ብሎ ንጥረ-ነገሩን አመጣ።

መድኃኒቱ የጎንዮሽ ተፅዕኖ ይኑረው አይኑረው አልተፈተሸም። የለንደን ማራቶን ሁለት ቀን ሲቀረው ሞ ፋራህ መድኃኒቱን አራት ጊዜ በየሁለት ሰዓቱ ተወጋ። ቢቢሲ ፓናሮማ እንዳረጋገጠው በወቅቱ መድኃኒቱን የወሰደ ብቸኛው እንግሊዛዊ አትሌት ሞ ፋራህ ነው።

አትሌቶች ምርመራ ሲደረጋላቸው ባለፉት ሰባት ቀናት የወሰዷቸውን የትኛውም ዓይነት መድኃኒቶች መዘርዘር አለባቸው። ፋራህ መድኃኒቱን ከተወጋ ከስድስት ቀናት በኋላ ነው የተመረመረው። ሌሎች የወሰዳቸውን መድኃኒቶች ዝርዝር ሲጠራ ኤል-ካርኒታይን የተሰኘውን መድኃኒት ግን ሳይጠቅስ ቀረ።

«እርግጠኛ ነህ ኤል-ካርኒታይን አልወሰድክም?» ተብሎ በተደጋጋሚ የተጠየቀው ሞ አልወሰድኩም ሲል ካደ። «እርግጠኛ ነህ በመርፌ አልወሰድክም?»፤ ሞ ፋራህ «ኧረ በጭራሽ» ሲል መለሰ።

ፋራህ ከቃለ-መጠይቁ ሲወጣ ከአሰልጣኙ ፋጅ ጋር ይገናኛል። ከዚያም ወደ መርማሪዎቹ መጥቶ «ይቅራታ ረስቼው ነው። ለካ ወስጃለሁ» ሲል ይናዘዛል።

ጉዳዩን እንዲያብራራ በቢቢሲ ፓኖራማ የተጠየቀው ሞ ፋራህ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። የሯጩ ጠበቃዎች በላኩት ደብዳቤ 'ኤል-ካርኒታይን መውሰድ የተከለከለ አይደለም። የተፈቀደውን መጠን እስካልተላለፍን ድረስ' ሲሉ መልሰዋል።

አክለውም 'ሞ ሁሌም ምርመራ ያደርጋል። በወቅቱ ባለማስታወሱ ነው ሳይናገር የቀረው። ተመልሶ ገብቶም ጉዳዩን አብራርቷል' ብለዋል።

የዩኬ አትሌቲክስ የበላይ አካል ከሰሞኑ ከሳላዛር ጋር በተገናኘ የተፈጠረውን ጉዳይ የሚያስረዳ መግለጫ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል።