ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሶማሊያዊያንን ለማቀራረብ የሚያደርጉት ጥረት እንቅፋት ገጥሞታል

የሶማሊያው ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በሶማሊያው ፕሬዝዳናንትና እራሷን ነጻ አገር አድርጋ ካወጀችው ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት መካከል መቀራረብን ለመፍጠር እያደረጉት ያለው ጥረት እንቅፋት እንደገጠመው ኢስት አፍሪካን የተባለው ጋዜጣ ዘገበ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጋር ሆነው የሶማሊላንድ ዋና ከተማ የሆችውን ሐርጌሳን ለመጎብኘት የነበራቸው ዕቅድ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ጋዜጣው እንደዘገበው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የቀረበው የጉብኝት ሃሳብ በሶማሊያና በሶማሌላንድ አስተዳዳሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ዓላማ ያደረገ ነው።

በሶማሊያ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰና ማዕከላዊው መንግሥት ከወደቀ በኋላ ሶማሌላንድ በሌሎች አገራት ወይም ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ይፋዊ እውቅና ባታገኝም የእራሷን ነጻ መንግሥትነት በማወጅ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥትን አቋቁማ ትገኛለች።

በዚህ ወር መጀመሪያ አዲስ አበባ ውስጥ የተካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ "ፋርማጆ" እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲን በጽህፈት ቤታቸው ጋብዘው አገናኝተዋቸዋል።

በዚህ ጊዜም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት እንደ አውሮፓዊያኑ በ1980ዎቹ ሶማሌላንድ ውስጥ ስለተፈጸመው ጭፍጨፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።

የሶማሌላንዱ ፕሬዝዳንትም የቀረበውን የይቅርታ ጥያቄ የተቀበሉት ቢሆንም፤ ለአገራቸው የምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት ግን የፋራማጆ ጉብኝት ጥያቄ "ግራ አጋቢ ነው" ብለዋል።

የሶማሌላንድ ምክትል ሚኒስትር ሊባን ዩሱፍ ኦስማን በዚህ ጉዳይ ላይ ሰጡ በተባለው ምላሽ ላይም ጉብኝቱ የማይሆን ነገር እንደሆነ አመልክተዋል።

"ፋራማጆ በሶማሌላንድ ሪፐብሊክ የሚያደርጉት ጉብኝት ፈጽሞ የማይሆን ህልም ከመሆኑ በተጨማሪ የማይሳካ ዕቅድ ነው" ብለዋል ሚኒስትሩ።