የሌሴቶው ጠቅላይ ሚኒስትር በቀድሞ ባለቤታቸው ግድያ ያለመከሰስ መብቴ ይከበርልኝ እያሉ ነው

የሌሴቶው ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔና ባለቤታቸው

የፎቶው ባለመብት, Molise Molise/Lesotho Times

የሌሴቶው ጠቅላይ ሚኒስትር በቀድሞ ባለቤታቸው ግድያ ሊጠየቁ እንደማይችሉ ከሰሞኑ ጠበቆቻቸው አስረድተዋል።

ለዚህም እንደ መከራከሪያ ያነሱት ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባላቸው ስልጣን ያለመከሰስ መብት ስላላቸው ነው።

ሁኔታውም ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተመርቷል፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የአሁኑ ባለቤታቸው ማሳየህ ታባኔ በግድያው ክስ ተመስርቷባቸዋል።

የቀድሞ ባለቤታቸው ሊፖሌሎ ታባኔ በሽጉጥ የተገደሉት ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖለቲካዊ ባልሆነና ከቤት ውስጥ ግድያ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት መቅረባቸው በስልጣን ላይ ያሉ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ያደርጋቸዋል።

ሁኔታው በደቡብ አፍሪካ ተከባ የምትገኘውን ትንሿን ሌሴቶ ያስደነገጠ ሆኗል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠበቃ ኳሌሃንግ ሌትሲካ እንዳሉት "ደንበኛዬ በስልጣን ላይ እያሉ ሊከሰሱ አይችሉም። ይህ ማለት ግን ከሕግ በላይ ናቸው ማለት አይደለም" ብለዋል።

የሕገ መንግሥት ትርጓሜን የሚሰጠው ፍርድ ቤት ያለመከሰስ መብታቸውን በተመለከተ ውሳኔ ሊያስተላልፍ ይገባል በማለትም ጠበቃቸው ተከራክረዋል።

ጉዳያቸውን ሲያይ የነበረው ፍርድ ቤትም ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ይይ ሲል አስተላልፎታል።

የ80 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት መቅረብ ቢኖርባቸውም ደቡብ አፍሪካ ለህክምና በመሄዳቸው ምክንያት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

ይህንንም ተከትሎ ከአገር ኮብልለው ነው ቢባልም እሳቸው ግን አስተባብለዋል። በጥር ወር ፖሊስ የአርባ ሁለት ዓመት እድሜ ያላቸውን የአሁኗን ባለቤታቸውን ጠርጥሬያለሁ ማለቱን ተከትሎ፤ ቀዳማዊቷ እመቤቷ ጠፍተው ነበር።

ፖሊስም በምላሹ የእስር ማዘዣ አውጥቶ ደቡብ አፍሪካ በመሄድ ከጠበቃዎቻቸውና ከፓሊስ ጋር በተደረገ ድርድር እጃቸውን መስጠታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ባለፈው ወር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግድያው ጋር በተያያዘ በፖሊስ መጠየቃቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ደጋፊዎች በመዲናዋ ማሴሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንዲለቁ በሰልፍ ጠይቀዋል።

የተቃዋሚዎች ግፊት በመጨመሩም ስልጣን እንደሚለቁ ቢያሳውቁም መቼ ሊሆን እንደሚችል አላሳወቁም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤታቸውም ሆነ እሳቸው የተወነጀሉበትን ወንጀል ከማንሳት ተቆጥበው በጡረታ ራሴን አገልላሁ ብለው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Lesotho Times

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞ ባለቤት ሊፖሌሎ ታቤን በሌሴቶ መዲና ማሴሮ በሚገኘው ቤታቸው ጥይት ተተኩሶባቸው የተገደሉት ከሦስት ዓመት በፊት ነበር።

በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለበዓለ ሲመታቸው ሁለት ቀናት ሲቀራቸው ነበር ግድያው የተፈጸመው ተብሏል፤ መረር ያለ የፍች ሂደትም ላይ ነበሩ።

በወቅቱም ከአሁኗ ባለቤታቸው ጋር አብረው ይኖሩ ነበር ተብሏል።

ነገር ግን ሊፖሌሎ በወቅቱ ቀዳማዊት እመቤት ማን ተብሎ ይጠራ የሚለውንም ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ወስደውት፤ የቀዳማዊ እመቤት ለሳቸው ይገባል በሚል ተወስኗላቸው ነበር።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለበኣለ ሲመታቸው ሁለት ቀን ሲቀራቸው በመገደላቸው ምክንያት የአሁኗ ባለቤታቸው በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል።

ከሁለት ወራት በኋላም ከአሁኗ ባለቤታቸው ጋር በሮማውያን ካቶሊክ ስነ ስርአት መስረት ጋብቻቸውን ፈፀሙ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቀዳማዊቷ እመቤት ማሳየህ ታባኔ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀድሞ ባለቤት ክስ ተመስርቶባቸው በ2ሺ ብር ዋስ ወጥተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ቀዳማዊቷ እመቤት የቤተሰቡ ቅርብ የሆነውን ታቶ ሲቦላን በመግደል ሙከራም ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ታቶ ሲቦላ በወቅቱ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሲገደሉ የአይን እማኝ ነበርም ተብሏል።

ማሳየህ እስካሁንም የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ አልተጠየቁም።