አቶ ንዋይ ገብረአብ በሚያውቋቸው አንደበት

አቶ ንዋይ ገብረአብ

የፎቶው ባለመብት, የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ

ለረዥም ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የየቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊና አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢኮኖሚ አማካሪ ሆነው ያገለገሉት አቶ ንዋይ ገብረአብ ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ከ1970ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና በፕላን ኮሚሽን ውስጥም ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል። ከኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪነታቸው ባለፈ የኢትዮጵያ የልማት ጥናት ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።

በተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥም በአማካሪነት ሰርተዋል። አቶ ንዋይ ከአዲስ አበባ እና ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።

" በአገሪቱ ይመዘገቡ ለነበሩ የኢኮኖሚ እድገቶች መንግስትንና አቶ መለስን በማማከር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል" ዶ/ር አብረሃም ተከስተ

የቀድሞው የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ዶ/ር አብረሃም ተከስተ አሁን የትግራይ ክልል የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊእንደሚያስታውሱት የኢትዯጵያ ኢኮኖሚ በደርግ ጊዜ በ80ዎቹ መጀመርያ በተለይ ኢኮኖሚው የተሽመደመደበትና ቀውስ ውስጥ የወደቀበት ጊዜ ነበር። ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣና እርሳቸው በአማካሪነት ሥራ ሲጀምሩ አንዱ ትልቁ ፈተና ኢኮኖመሚውን ማረጋጋት ነበር። የወጪ ንግድ፣ የመንግሥት በጀት የነበረውን ክፍተት፣ ትልልቅ የአገሪቱ የኢኮኖሚው ችግሮችን፤ የውጭ እዳን ጭምር ሥርዓት እንዲይዝ ያደረጉት አቶ ንዋይ መሆናቸውን ይናገራሉ። በዚህ ረገድ አቶ ንዋይ የተጫወቱት ሚና ትልቅ ነበርም ይላሉ።

እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጀት አይኤም ኤፍ፣ ዓለም ባንክ ጋር በነበረ ድርድር ከፊት ሆነው ይደራደሩ የነበሩት እርሳቸው እንደነበሩና የኢትዯጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ ብዙ መጣራቸውንም ያስታውሳሉ ዶ/ር አብረሃም። "አቶ ነዋይ አገሩቱን የሚጠቅሙ ወሳኝ ፖሊሲዎችን ተከላክለዋል። በአጠቃላይ በአገሪቱ ይመዘገቡ ለነበሩ የኢኮኖሚ እድገቶች መንግስትንና አቶ መለስን በማማከር ትልቅ ሚና ተጫውተዋል"ይላሉ።

ከሰው ጋር ተረዳድቶ መስራት የሚችሉ ፣ ይህ ሁሉ እውቀት ይህንን ሁሉ ልምድ ይዘው እጅግ ትሁት፣ ሰው እንዲማር ሰው እንዲያድግ የሚወዱ ቀና ሰው ናቸው ሲሉም ይገልጿቸዋል አቶ ንዋይን። መንግሥት የራሱ የፖሊሲ ነፃነት እንዲኖረው ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንም ይጠቅሳሉ።

"እጅግ ረጋ ያሉ፣ ለምንም ነገር የማይቸኩሉ፣ በጥሞና አስተውለው የሚናገሩ ሰው ናቸው" ዶ/ር ግሩም አበበ

ዶ/ር ግሩም አበበ በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት (EDRI) መሪ ተመራማሪ ነበሩ። አቶ ንዋይን ላለፉት 13 ዓመታት ያውቋቸዋል። መጀመሪያ ሲተዋወቁ ያስተዋሉት "እጅግ ረጋ ያሉ፣ ለምንም ነገር የማይቸኩሉ፣ በጥሞና አስተውለው የሚናገሩ ሰው እንደሆኑ ነው" ይላሉ።

የሚናገሩት ነገር ጠንካራ፣ ፍሬያማና አስተማሪ እንደነበረ ያስታውሳሉ። "ጠንከር ያለ መልዕክት ማስተላለፍ እንኳን ሲፈልጉ ረጋ ብለው፣ የተመረጡ ቃላት ተጠቅመው፣ መልዕክቱ ሌላ ይዘት እንዳይሮረው አድርገው ነበር" ሲሉም ይገልጿቸዋል።

አንድ ወቅት ለልምድ ልውውጥ ወደ ደቡብ ኮርያ አንድ ላይ አቅንተው ነበር። አብዛኛው ግንኙነታቸው ሥራ ተኮር ቢሆንም፤ የደቡብ ኮርያው አጋጣሚ ከሥራ ውጪ የመነጋገር እድል ሰጥቷቸው ነበር።

"የብዙ አገር ልምድ ያላቸው፣ በጣም ብዙ ያነበቡ፣ ያነበቡትን ለአገሬ በምን መልኩ ይጠቅማል የሚለው የሚያስጨንቃቸው ሰው እንደሆኑ ተረዳሁ" ሲሉ በወቅቱ ስለ አቶ ንዋይ የተሰማቸውን ዶ/ር ግሩም ይናገራሉ።

በደቡብ ኮርያው መድረክ፤ ስለ ምሥራቅ እስያ አገራት ምጣኔ ኃብት የተለያዩ ምሁራን ንግግር ያደርጉ ነበር። "አቶ ንዋይ ያደሩትን ንግግር፣ ለሚጠየቁት ጥያቄ የሰጡት መልስ ሁላችንንም አስገርሞን ነበር" ሲሉም ትውስታቸውን ለቢቢሲ አካፍለዋል።

በመሰረቱት የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት አጥኚዎችን ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምረው መልምለው፣ ትምህርት እንዲማሩ፣ በአግባቡ ከተማሩ እገዛ ማድረግ እንደሚችሉ የሳስቡ እንደነበርም ያስታውሳሉ።

"ኢንስቲትዩቱን ሲያቋቁሙት አላማዬ ብለው የያዙት ጠንካራ የሰው ኃይል መፍጠርና ያንን የሰው ኃይል ተጠቅሞ አገሪቷን በፖሊሲ፣ በምርምር መርዳት የሚችል ተቋም እንዲሆን ነው።"

ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፍ ተቋሞች በጥናትና ምርምር ዘርፍ በሚያወጡት የደረጃ ሰንጠረዥ ከኢትዮጵያ አንደኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ከአንድ እስከ አስር ደረጃ እንደሚያገኝም ይናገራሉ። በአጭር ጊዜ ኢንስቲትዩቱን እዚህ ደረጃ ማድረስን እንደ ትልቅ ስኬትም ያዩታል።

"ወጣት ሆነው የመለመሏቸው የሳቸው ፍሬ የሆኑ ልጆች የተለያየ ቦታ አሉ። በዚህ በጣም ደስ እንደሚላች እሰማለሁ።"

በአህጉሪቱ በአጠቃላይ ጠንካራ የምጣኔ ኃብት ፖሊሲ እንዲኖር እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሚካሄዱ ድርድሮችን በበቂ ሁኔታ ለመምራት (እኩል ተደራዳሪ ለመሆን) በቂ አገር በቀል የተማረ ኃይል ሊኖር እንደሚገባ ያምናሉ።

አቶ ንዋይ ከሥራ ውጪ ባለ ሕይወታቸው መጻሕፍት ከማንበብ ባሻገር ሂልተን ሆቴል አካባቢ ቅዳሜና እሑድ ጋዜጣ ማንበብ ያዘወትሩ እንደነበር ዶ/ር ግሩም ይናገራሉ። ከተለያዩ አገራት ልምድ ለመቅሰም ስለሚሹ ዓለም አቀፍ የውይይት መድረኮችን መከታተልም ይወዱ ነበር።

ዶ/ር ግሩም እንደሚሉት ለመጨረሻ ጊዜ የተነጋገሩት ከስድስት ወር በፊት ነበር። በወቅቱ አቶ ንዋይ ጡረታ ወጥተው መጽሐፍ እየጻፉ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ግሩም "መጽሐፍዎ በእጄ እስከሚገባ እጓጓለሁ" እንዳሏቸው ያስታውሳሉ።

በወቅቱ አቶ ንዋይም "መጽሐፉን እየሠራሁበት ነው" ብለው ምላሽ ሰጥተዋቸው ነበር።

"በጣም ለስላሳ ሰው፣ ረጋ ያሉ፣ ባለራዕይ፣ ነገሮችን ራቅ ብለው ማየት የሚችሉ"ዶ/ር ፍሬው በቀለ

ትውውቃቸው የጀመረው ተመርቀው የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩትን ሲቀላቀሉ ሲሆን በወቅቱም አቶ ንዋይ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ነበሩ። በወቅቱ ለትምህርት ተልከው ስለነበር፤ የመስሪያ ቤቱ ድጋፍም አልተለያቸውም ግንኙነታቸውም የቀጠለው በዚያ መልኩ ነው። ተምረው ከመጡ ከ2013 በኋላ በጡረታ እስከተገለሉበት ድረስ አብረው ሰርተዋል። አብዛኛውን ጊዜ ከስራ ጋር በተገናኘ ሁኔታ በተለይም ከምጣኔ ኃብት ጋር በተያያዘ ውይይትም አድርገዋል። አቶ ንዋይን እንዴት ይገልጿቸዋል ሲባሉም "በጣም ለስላሳ ሰው፣ ረጋ ያሉ፣ ባለራዕይ፣ ነገሮችን ራቅ ብለው ማየት የሚችሉ" ይሏቸዋል።

ለአምስት አመታትም ያህል ከአቶ ንዋይ ጋር በቅርበት የመስራት እድሉን አግኝተዋል።

ለዚህም የሚያነሱት ተማሪዎችን በሚመለምሉበት ወቅት አስር፣ ሃያ አመት ወደፊት የሚሆነውንም በማሰብ ነበር። በተለይም ለምርምሮች ከፍተኛ ቦታንም ይሰጡ እንደነበር ያስታውሳሉ።

"ለውይይቶች ክፍት ነበሩ፤" የሚሏቸው አቶ ንዋይ በተደጋጋሚ አፍሪካውያን ከውጭ የሚመጡ ጫናዎችን ተቋቁመው የራሳቸውን የምጣኔ ኃብትም ሆነ ሌሎች ፖሊሲዎቻቸውን ለነሱ በሚመጥን መልኩ ሊቀርፁ ይገባል በማለት በተደጋጋሚ ይሟገቱ ነበርም ያስታውሳሉ።

"ባለ ራዕይ ናቸው ስል ለፖሊሲ አውጭ ዛሬ የገጠመ ችግር ብቻ አይደለም ምርምር የወደፊቱንም ያለመ ነው። ለታዳጊ ሃገር እንደዚህ አይነት ነገሮች ብዙ ላይታሰቡ ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት የሚደረገው የእለት ተእለትና አጣዳፊ ለሆኑ ጉዳዮች ነው።" የሚሉት ዶ/ር ፍሬው ከዛ ባለፈ ግን የወደፊቱን የሚሆነውንም የሚቀይሱ ናቸው ይሏቸዋል አቶ ንዋይን።