ታዋቂው የሆሊውድ ሰው ሃርቪ ዋይንስታይን በወሲባዊ ቅሌት ዘብጥያ ወረደ

Former Hollywood producer Harvey Weinstein arrives at court on Monday

የፎቶው ባለመብት, EPA

ሃርቪ ዋይንስታይን የተሰኘው ጉምቱ የሆሊውድ ሰው በአስገድዶ መድፈር እና በሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶች ጥፋተኛ ሆኖ ተገኘ።

የ67 ዓመቱ ዋይንስታይን፤ ኒው ዮርክ በሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት ወስጥ ነው በሦስተኛ ደረጃ የአስገድዶ መድፈር እና በአንደኛ ደረጃ ወሲባዊ ጥቃት ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው።

ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ በተገኘባቸው ወንጀሎች ቢያንስ የ25 ዓመት እሥር ሊጠብቀው ይችላል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪም ካሊፎርኒያ በተሰኘችው ግዛት ሁለት ሴቶች ላይ ፈፅሟል በተባለው ጥቃት ተጠርጥሮ ይፈለጋል።

ለበርካታ ዓመታት ሆሊውድን የዘወረው ዋይንስታይን 80 ያክል ሴቶች ጥቃት አድርሶብናል ሲሉ ይወነጅሉታል። ታዋቂዎቹ ተዋንያት ገዌኔዝ ፓልትሮው፣ ኡማ ትሩማን እና ሳልማ ሃዬክን ጨምሮ በርካቶች ግለሰቡ ጥቃት አድርሶብናል ሲሉ ምስክርነት ሰጥተዋል።

#MeToo የተሰኘው የማሕበራዊ ሚድያ ቅስቅሳ የተጀመረው ዋይንስታይን ጥቃት አድርሶብናል ያሉ ሴቶች ወደ ፊት መውጣት ከጀመሩ በኋላ ነው።

ዝናን ያተረፉ ፊልሞችን በዋና አዘጋጅነት የመራው ሃርቪ ለኦስካር ሽልማት የበቁ እንደ 'ጉድ ዊል ሃንቲንግ'፣ 'ዘ ኪንግስ ስፒች' እና 'ፐልፕ ፊክሽን' የተሰኙ የጥበብ ሥራዎችን አምርቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ጄሲካ ማን [ግራ] እና አናቤላ [ቀኝ] ዋይንስታይንን በአስገድዶ መድፈር የከሰሱ ናቸው

ፍርዱ ከተሰጠ በኋላ የደረት ሕመም የገጠመው ዋይንስታይን ኒው ዮርክ ወደሚገኝ አንድ ሆስፒታል መወሰዱ ተዘግቧል።

ግለሰቡ ፍርድ እስኪሰጠው ድረስ 'ሪከር' የተሰኘች ደሴት ላይ ባለ አንድ እሥር ቤት እንዲቆይ ይደረጋል ተብሏል።

የቀረቡበትን ክሶች በሙሉ የሚክደው ዋይንስታይን የሥራ አጋሩ የነበረችው ሚሚ ሄሊ ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈፅሟል፤ የዛሬ 7 ዓመት ደግሞ ጄሲካ ማን የተሰኘች መፃኢ ተዋናይትን አስገድዶ ደፍሯል ተብሎ ነው ወንጀለኛ የተባለው።

የግለሰቡ ጠበቃዎች ደንበኛችን ንፁህ ስለሆነ መሟገታችንን እንቀጥላለን ይላሉ። አልፎም በተሰጠው ፍርድ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ አሳውቀዋል።

ዋይንስታይን ኒው ዮርክ ውስጥ ከቀረበበት ክስ ባለፈ ካሊፎርኒያ ውስጥ ሌላ ክስ ይጠብቀዋል። ሃርቪ ዋይንስታይን ጥቃት አድርሶባቸዋል የተባሉ ሴቶች የገንዘብ ካሳ እንሚያገኙም ይጠበቃል።