ኮሮናቫይረስ፡ የመጀመሪያውን የቫይረሱን ተጠቂ ማግኘት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ከምናስበው በላይ

የህክምና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ የሞተ ሰውን አስከሬን ሲያወጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቻይና ባለሥልጣናት እና ባለሙያዎች የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ተጠቂን ለማግኘት እየተሯሯጡ ነው።

'ፔሸንት ዜሮ' የተሰኘውን የመጀመሪያውን ተጠቂ የማግኘት 'ሚሽን' ቀጥሏል። ግን በሽተኛውን ማግኘት ለምን አስፈለገ?

'ፔሸንት ዜሮ' አንድ በሽታ ሲከሰት የመጀመሪያው ተጠቂን ለመለየት የሚጠቀሙበት ቃል ነው። አንድ ወረረሽኝ ሲከሰት የመጀመሪያውን የቫይረስ ወይም ባክቴሪያ ተጠቂ ማግኘት ወሳኝ ነው። ይህም ከየት፣ ወዴት እና እንዴት የሚሉ ጥያቄዎችን ይመልሳል።

እነኚህን ጥያቄዎች መመለስ ቫይረሱ ወይም ባክቴሪያው እንዳይዛመት፤ እንዲሁም መድኃኒት እንዲገኝለት ያገዛል።

የኮሮኖቫይረስ የመጀመሪያ ተጠቂ ይታወቃል? መልሱ - አይታወቅም ነው።

የቻይና ባለሥልጣናት የመጀመሪያ የኮሮና ቫይረስ ክስተት ሪፖርት የተደረገው ታኅሳስ 2012 ውስጥ ነው ይላሉ። የኒሞኒያ አይነት ባሕርይ ያለው ኮሮና መጀመሪያ የተከሰተባት ቦታ ሁቤይ ግዛት ውስጥ የምትገኘው ዉሃን ከተማ ናት። በሽታው ዉሃን ውስጥ የሚገኝ አንድ ቄራ ውስጥ እንደጀመረም ይገመታል።

አሁን ላይ ከተመዘገው 75 ሺህ የበሽታው ተጠቂ መካከል 82 በመቶው ምንጩ ከዉሃን ከተማ ውስጥ ነው።

ነገር ግን የቻይና አጥኚዎች ይፋ ያደረጉት አንድ ጥናት እንደሚያትተው በኮቪድ-19 የተጠቃው የመጀመሪያው ሰው የታየው ኅዳር 21/2012 ነው። ይህ ሰው ደግሞ ወደ ሥጋ መሸጫው ቄራ አልሄደም።

ጉምቱው ዶክተር ዉ ዌንጁዋን የመጀመሪያ የተመዘገበ ተጠቂ አንድ ሸምገል ያሉና የመርሳት በሽታ ያለባቸው ሰው ናቸው ሲሉ ለቢቢሲ የቻይና አገልግሎት ተናግረዋል።

«የባሕር እንስሳት ሥጋ ከሚሸጥበት ሥፍራ ራቅ ብሎ የሚኖር ሰው ነው። በሽተኛ ስለሆነ ደግሞ ወደ ውጭ አይወጣም።»

ዶክተሩ አክለው እንደሚናገሩት ሌሎች ሦስት ሰዎች በሚቀጥሉት ቀናት ተመሳሳይ ምልክት አሳዩ። ከሦስቱ ሁለቱ ወደ ቄራው ብቅ ብለው የማያውቁ ናቸው።

ቢሆንም አጥኚዎቹ ያገኙት መረጃ እንደሚያሳየው በመጀመሪያዎቹ ቀናት ወደ ሆስፒታል መጥተው ከተመረመሩ 41 ሰዎች መካከል 27ቱ ወደ ቄራው ሄደዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፤ በሽታው መጀመሪያ ከእንስሳ ወደ ሰው ተላለፈ። ከዚያ ከሰው ወደ ሰው ተዛመተ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ አሁንም ይሠራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የኢቦላ ቫይረስ የተቀሰቀሰው በአንድ የሁለት ዓመት ሕፃን ልጅ እንደሆነ ይነገራል

አንድ ሰው ወረርሽኝ መቀስቀስ ይችላል?

በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2014 ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ ድጋሚ ተከስቶ እስከ አሜሪካ የደረሰው የኢቦላ ቫይረስ የ11 ሺህ ሰዎችን ህይወት እንደቀጠፍ ይታመናል። አልፎም 28 ሺህ ሰዎችን በክሏል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ዘግቧል።

ሳይንቲስቶች ቫይረሱ የተነሳው ከአንድ ሰው ነው ይላሉ - ከአንድ የሁለት ዓመት ጊኒያዊ ጨቅላ። አክለውም ጨቅላው የሌሊት ወፎች ከሠፈሩበት ዛፍ ቫይረሱን ሳያገኝ አይቀርም ይላሉ።

የመጀመሪያዋ 'ፔሸንት ዜሮ' ሜሪ ማሎን ትባላለች። ቅፅል ስሟም 'ታይፎይድ' ሜሪ ይባላል። ታይፎይድ ኒው ዮርክ ውስጥ በ1906 ላይ ሲከሰት አዛምታለች በሚል ነው ይህ ቅፅል ስም የተሰጣት።

በርካታ የጤና ባለሙያዎች የመጀሪያ የበሽታ ተጠቂ የሆነን ሰው ማንነት ይፋ ማድረግ አይፈልጉም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የተሳሳተ መረጃ እንዳይሰራጭ ካለ ፍራቻ ነው። ከዚያም ሲያልፍ 'ፔሸንት ዜሮ' የተሰኘው ግለሰብ ላይ መገለል እንዳይደርስ በማሰብ ነው።

ለምሳሌ ኤድስ ሲከሰት የመጀመሪያው ተጠቂ ተብሎ የታወጀው ሰው በስህተት ነበር ስያሜውን ያገኘው። ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ነው ሳይንቲስቶች ግለሰቡ የመጀሪያው እንዳልሆነ ያሳወቁት።

ወጣም ወረደ የመጀመሪያውን ተጠቂ ማግኘት እጅግ አስፈላጊ ነው ይላሉ አጥኚዎች። ከዚህ ተጠቂ ታሪክ በመነሳት ደግሞ ለሽታው መድኃኒት የመሥራት ዕድል ሊኖር ይችላልና።