ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርኔት ሲቋረጥ ምን ይከሰታል?

ወጣት ልጅ ስልኩ ላይ እየተየበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ማርቆስ ለማ ከቢሮው መስኮት ሆኖ አዲስ አበባን እየቃኛት ነው። ቢሮው የሚገኝበት ቦታ የአዲስ አበባን ውብ ገጽታ በቀላሉ ያሳየዋል። ማርቆስ አይስአዲስ የተሰኘ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ተቋም መስራች ነው።

ከሌሎች ጋር ተጋርቶ የሚሰራበት ቢሮው ለሥራ ፈጠራ በነቁ እና በጥቁር ቡና በተነቃቁ የፈጠራ ባለሙያዎች የተሞላ ነው።

ይህ የፈጠራ ባለሙያን መሰባሰቢያ ግን የሰው ዘር ዝር ሳይልበት የሚቀርበት ወቅት አለው-ኢንተርኔት ሲቋረጥ።

አክሰስ ናው የተባለ የዲጂታል መብት ተሟጋች ለቢቢሲ ያጋራው መረጃ እንደሚያሳየው እአአ በ2019 ብቻ በ33 አገራት ይኹነኝ ተብሎ 200 ጊዜ ያህል ኢንተርኔት ተቋርጧል።

"እዚህ ሰው መምጣት ያቆማል፤ ማንም ድርሽ አይልም፤ ቢመጡም አንኳ ለረዥም ጊዜ አይቆዩም። ምክንያቱም ያለ ኢንተርኔት ምን ሊሰሩ ይችላሉ?" ሲል ይጠይቃል ማርቆስ።

"ሶፍትዌር ዴቬሎፕ የማድረግ ኮንትራት ተቀብለን በወቅቱ ማስረከብ ባለመቻላችን ተነጥቀናል። ምክንያቱም የኢንተርኔት መቋረጥ ነበር። ዓለም አቀፍ ደንበኞቻችንም እነርሱን ገሸሽ የሚያደርግ አገልግሎት እንዳለን ያስባሉ፤ ነገርግን ምንም ማድረግ አንችልም።"

በስልክ ትዕዛዝ ተቀብለው የሚያደርሱ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች በስልካቸው ትዕዛዝ እስኪመጣ ተሰባስበው ይጠብቃሉ። ነገር ግን "ኢንተርኔት በሌለበት ማን በኦንላየን ወይም መተግበሪያ ተጠቅሞ ማዘዝ ይችላል?" ይላል ማርቆስ።

"እዚህ ኢንተርኔት መዘጋት በንግድ ተቋማትና በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ አለው።"

የፎቶው ባለመብት, Markos Lemma

የምስሉ መግለጫ,

ማርቆስ ለማ ከድርጅቱ አይስአዲስ አርማ ጎን

ኢንተርኔትን ማቋረጥ

ኢንተርኔት ማቋረጥ በኢትዮጵያ ብቻ የሚከሰት የንግድ ሥራን ብቻም የሚያስተጓጉል አይደለም። አክሰስ ናው የተሰኘው ቡድን በሰራው ጥናት በዓለም ላይ የኢንተርኔት መቋረጥ በአስር ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተለያየ ምክንያት የጎዳ ሲሆን በዓለም የተለያዩ ስፍራዎችም ላይ ይከሰታል።

መንግሥታት የተወሰነ አካባቢ ኢንተርኔት እንዳያገኝ ሲፈልጉ የኢንተርኔት አቅራቢው ተቋም ባልቦላውን እንዲያጠፋ ያዛሉ፤ አልያም ደግሞ የተወሰነ የድረገጽ አገልግሎትን ብቻ እንዳይሰራ ያደርጋሉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንዲህ አይነት እርምጃዎች መንግሥታት ጭቆናን የሚያካሂዱበት መሳሪያ ነው በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የመብት ተሟጋቹ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ኢንተርኔት መቋረጥ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በሚበረታባቸው ወቅቶችና አካባቢዎች ላይ ጎልቶ ይታያል።

በ2019 ብቻ ኢንተርኔት የተቋረጠባቸው አገራት ሲጠኑ 60 ህዝባዊ ተቃውሞዎች በነበረበት ወቅት 12ቱ ደግሞ በምርጫ ጊዜ መሆናቸውን ያሳያል።

መንግሥታት አንዳንዴ ኢንተርኔት የተቋረጠው የሕዝብ ደህንነትን ለማረጋገጥ እና ሐሰተኛ ዜና እንዳይዛመት ለመከላከል እንደሆነ በመግለጽ ድርጊቱን ያስተባብላሉ።

ይህንን ሃሳብ የሚቃወሙ አካላት ግን የመረጃ ፍሰትንና የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለማጨናገፍ ሆን ተብሎ የሚጠቀሙበት መንገድ መሆኑን በመግለጽ ይተቻሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ኢንተርኔትን የማግኘት መብት ሰብዓዊ መብት ነው ብሎ የደነገገው እኤአ በ2016 ነው። ነገር ግን ሁሉም የዓለማችን መሪዎች የዚህ ሃሳብ ደጋፊዎች ወይም አቀንቃኞች አይደሉም።

እኤአ በ2019 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ኢንተርኔት "ውሃ ወይንም አየር አይደለም" በማለት የኢንተርኔት መቋረጥ የአገር መረጋጋትን ለማረጋጋጥ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ ተናግረው ነበር።

ማርቆስ ለማ በዚህ ሀሳብ በጣም ነው የሚበሳጨው።

"መንግሥት ኢንተርኔትን እንደ አስፈላጊ ነገር አያየውም። ኢንተርኔትን እንደ ማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ብቻ ነው የሚያየው፣ ስለዚህ የኢንተርኔትን ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳውን አይመለከቱትም።"

በብዛት ኢንተርኔትን በማቋረጥ ህንድ ቀዳሚ ናት

የባለፈው የፈረንጆች ዓመት መረጃ እንደሚያመለክተው በዓመቱ ከየትኛውም አገር በበለጠ ህንድ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በተደጋጋሚ ኢንተርኔትን የመዝጋት ሁኔታ ተከስቷል።

የሞባይል ኢንተርኔትና የብሮድባንድ አገልግሎቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ለ121 ጊዜ እንዲዘጉ ተደርገዋል። አብዛኛው ማለትም 67 በመቶው ደግሞ ያጋጠመው በህንድ በምትተዳደረው በአወዛጋቢዋ የካሽሚር ግዛት ውስጥ ነው።

የማዕከላዊ አፍሪካ አገር የሆነችው ቻድ ደግሞ እስካሁን ከታዩት የኢንተርኔት ማቋረጦች መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን በማስተናገድ ቀዳሚ ሆናለች። በአገሪቱ በፈረንጆቹ 2018 ላይ የተዘጋው የኢንተርኔት አገልግሎት ከ15 ወራት በላይ ሳይከፈት ቆይቷል።

ሱዳንና ኢራቅ ውስጥ በተካሄዱ ተቃውሞዎች ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች በኢንተርኔት መዘጋት የተነሳ እንቅስቃሴያቸውን ሲያስተባብሩ የነበረው ከኢንተርኔት ግንኙነት ውጪ ሆነው ነበር።

የእያንዳንዱ ኢንተርኔትን የመዝጋት እርምጃ ከሚሸፍነው ቦታ አንጻር የሚኖረው ተጽእኖ የተለያየ ነው። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ውስን ከሆኑ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃንን የመዝጋት እርምጃ አንስቶ ሁሉንም የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ማቋረጥ የሚከሰትበት ሁኔታ አለ።

"ቶርቲንግ" የኢንተርኔት አገልግሎትን የመቆጣጠር አይነት እገዳ ሲሆን መከሰቱንም ለመከታተል አስቸጋሪው ነው። ይህም የሚከሰተው መንግሥታት የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ቀርፋፋ እንዲሆን በማድረግ ነው።

ይህም 4ጂ የነበረውን ፈጣኑን የኢንተርኔት ትስስር ወደ 2ጂ በማውረድ ቪዲዮዎችን ለማጋራት ወይም በቀጥታ ለማስተላለፍ ከማይቻልበት ደረጃ ያደርሰዋል።

ይህ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ታጂክስታን ውስጥ ፌስቡክን፣ ትዊተርንና ኢንስታግራምን ጨምሮ በአብዛኞቹ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ አጋጥሟል።

ሩሲያንና ኢራንን የመሳሰሉ አገራት ደግሞ በኢንተርኔት ላይ ያላቸውን ቁጥጥር ሊያጠናክር የሚያስችል በአገራቸው ውስጥ ብቻ ተወስኖ የሚሰራ የኢንተርኔተ አገልግሎትን እየገነቡና እየፈተሹ መሆናቸው ይነገራል።

የዲጂታል መብቶች ተከራካሪው አክሰስ ናው የተባለው ቡድን እንደሚለው "በርካታ አገራት የተቺዎቻቸውን ድምጽ ለማፈን ወይም ማንም ሳያይና ሳይሰማ ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመፈጸም ሲሉ የመጨረሻውን ኢንተርኔትን የመዝጋት እርምጃ ከሌሎች አገራት በመማር ተግባራዊ እያደረጉ ነው።"