የቀድሞ የግብጽ ፕሬዝደንት ሆስኒ ሙባረክ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ሆስኒ ሙባረክ

የፎቶው ባለመብት, KHALED DESOUKI

የቀድሞ የግብጽ ፕሬዝደንት ሆስኒ ሙባረክ በ91 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ሆስኒ ሙባረክ ህይወታቸው ያላፈው ግብጽ ካይሮ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው ሳለ ነው።

ሆስኒ ሙባረክ እ.አ.አ. 2011 ላይ በግብጽ የአረብ አብዮት ከተቀሰቀሰ በኋላ በአገሪቱ ጦር ከሰልጣናቸው እንዲነሱ ተደርገዋል።

የቀድሞ ፕሬዝደንት ግብጽን ለሦስት አስርት ዓመታት መርተዋል።

የአረብ አብዮት በተቀሰቀሰ ወቅት ለተቃውሞ በወጡ ሰልፈኞች ላይ በተወሰደው እርምጃ በተባባሪነት ተጠያቂ ተደርገው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸው ነበር።

ይሁን እንጂ ከሦስት ዓመት በፊት የተመሰረቱባቸው ክሶች ውድቅ ተደርገው ነጻ ወጥተው ነበር።

የቀድሞ ፕሬዝደንት ህልፈተ ህይወትን ይፋ ያደረገው የግብጽ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው።

ሙባረክ ከአንድ ወር በፊት የቀዶ ህክምና ማድረጋቸውን እና በጽኑ ህሙማን ማቆያ ውስጥ መቆየታቸውን የቤተብ አባሎቻቸው ለግብጽ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

ሙባረክ ከልጅ ልጃቸው ጋር በሆስፒታል ሳሉ የተነሱት ፎቶግራፍ በርካቶች ተጋርተውት ነበር።

ባሳለፍነው ቅዳሜ የሙባረክ የልጅ ልጅ የሆነው አላ፤ አያቱ በጽኑ ሕሙማን ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ አረጋግጦ ነበር።

እአአ 1928 የተወለዱት ሙባረክ፤ በወጣትነት እድሜያቸው የግብጽ አየር ኃይልን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ የአረብ-አስራኤል ጦርነት ወቅት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

ፕሬዝደንት አንዋር ሳዳት መገደላቸውን ተከትሎ ሙባረክ የግብጽ ፕሬዝደንት በመሆን መንበረ ስልጣኑን ይዘዋል።