የኢራን ምክትል ጤና ጥበቃ ሚንስቴር ኮሮናቫይረስ እንደያዛቸው ተገለጸ

የኢራን ምክትል ጤና ጥበቃ ሚንስትር ኢራጅ ሀሪርቺ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኢራን ምክትል ጤና ጥበቃ ሚንስትር ኢራጅ ሀሪርቺ ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ተገለጸ።

በአገሪቱ 15 ሰዎችን የገደለውን በሽታ በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተጣጣረች ሲሆን፤ ኢራጅ ሀሪርቺ ራሳቸውን አግልለው አስፈላጊውን ህክምና መውሰድ እንደጀመሩ ተናግረዋል።

ምክትል ጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ሰኞ እለት ስለ ኮቪድ-19 ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ፤ ግንባራቸውን በተደጋጋሚ ሲጠራርጉ ታይተው ነበር። በእለቱ የአገሪቱ ባለሥልጣናት የበሽታውን የስርጭት ስፋት በተመለከተ ሀሰተኛ መረጃ ሰጥተዋል መባሉን አስተባብለው ነበር።

እስካሁን 95 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል ቢባልም፤ ትክክለኛ ቁጥሩ ከዚህ ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው፤ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ድንገት ማሻቀቡ አሳሳቢ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የቀጠናው ዋና ዳይሬክተር ወደ ኢራን ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ የተሸጋገረ ሲሆን፤ የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ እንዳሉት፤ የቴክኒክና የጤና ባለሙያዎች ቡድን እንዲሁም የምርመራ መሣሪያ በቀጣይ ሁለት ቀናት ወደ ኢራን ይደርሳል።

እስካሁን በመላው ዓለም በኮቪድ-19 እንደተያዙ የተመዘገበው ሰዎች ቁጥር ከ80,000 በላይ ሲሆን፤ 2,700 ሰዎች ሞተዋል።

ከኢራን የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በኢራን መንግሥት ይፋ ከተደረገው አሀዝ ይበልጣል።

ኢራን በሽታው በተሰራጨባቸው አካባቢዎች ሰዎች ተለይተው የሚቆዩባቸው ሥፍራዎች እንደማታዘጋጅ አሳውቃለች። የኢራን ባለስልጣኖች ማቆያ ሥፍራዎችን "ኋላ ቀር ናቸው፤ አናምንባቸውም" ብለዋል።