ሳዑዲ አረቢያ ወደ አገሯ የሚደረጉ ሐይማኖታዊ ጉዞዎችን አገደች

ፊሊፒንስ Image copyright Getty Images

ሳዑዲ አረቢያ ለሐይማኖታዊ ጉብኝት የሚደረጉ ጉዞዎችን አግዳለች። አንድ ጃፓናዊት ለሁለተኛ ጊዜ በኮሮና መያዟ ተረጋግጧል። ሐምሌ ወር ላይ ሊካሄድ የታሰበለት ኦሎምፒክ 'ሊሰረዝ ይችላል' ተብሏል።

ሳዑዲ አረቢያ

የሳዑዲ መንግሥት የውጪ አገር ዜጎች ለሐይማኖታዊ ጉብኝት ወደ አገሩ እንዳይገቡ አገደ።

ይህ እገዳ ወደ መካ እና መዲና የሚደረጉ ሐይማኖታዊ ጉብኝቶችንም ያካትታል።

ሐምሌ ወር ላይ የሚደረገው የሃጂ ጉዞ በዚህ እገዳ ምክንያት ሊሰረዝ እንደሚችል ግን አልታወቀም።

ከዚህ በተጨማሪ ሳዑዲ አረቢያ ኮሮናቫይረስ ከተከሰተባቸው አገራት የሚመጡ ሰዎች ወደ ድንበሬ ድርሽ እንዳይሉ አደርጋለሁ ብለዋል።

ሳዑዲ እስካሁን በቫይረሱ የተያዘ ሰው አልተገኘም።

Image copyright European Photopress Agency

ጃፓን

በቫይረሱ ተይዛ የዳነችው ጃፓናዊት ሴት እንደገና በቫይረሱ ተያዘች።

የ40 ዓመት ሴት የሆነችው ጃፓናዊት ከሁለት ወር በፊት ነበር በቫይረሱ መያዟ ተረጋግጦ ወደ ሆስፒታል የገባቸው።

ለአንድ ወር ያክል በህክምና ላይ ቆይታ ከቫይረሱ መዳኗ ሲረጋገጥ ከሆስፒታል ትወጣለች። ይሁን እንጂ የመትንፈሻ አካል ህመም አጋጥሟት ወደ ሆስፒታል ስትሄድ ቫይረሱ በድጋሚ ተገኝቶባታል።

'ኦምፒክ ሊሰረዝ ይችላል' ተባለ

የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዲክ ፓዎንድ ለሬውተርስ ኦሊምፒክ ሊሰረዝ የማይችልበት ምክንያት የለም ሲሉ ተናገሩ።

የኮሚቴው አባል እንዳሉት የቫይረሱ ስርጭት 'ወረርሽኝ' ተብሎ የሚታወጅ ከሆነ እና ግልጽ የሆነ የጤና ስጋት የሚያስከትል ከሆነ ሊሰረዝ ይችላል ብለዋል።

የ2020 ኦሊምፒክን በጃፓን ቶኪዮ በወረሃ ሐምሌ ላይ ለማዘጋጀት እቅድ ተይዟል።

ቻናይ በአህዝ

የቻይና መንግሥት ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በየዕለቱ አዳዲስ አህዞችን ያወጣል።

እስከ ዕረቡ ምሽት ድረስ በቻይና ብቻ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 78497 ሲሆን የሟቾች ቁጥር ደግሞ 2744 ደርሷል።

የቻይና መንግሥት ቫይረሱን ለመቆጣጠር ለህዝቡ እያስተላለፈ ያለው መልዕክቶች ሦስት ናቸው። ከቤት አትውጡ፣ ሰብሰባዎች አታድርጉ እና ጉዞ አታድርጉ የሚሉ ናቸው።

በአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ

በአሜሪካና በደቡብ ኮሪያ መካከል ሊደረግ የነበረ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።

ደቡብ ኮሪያ በአንድ ምሽት ብቻ 334 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አስታውቃለች።

በትንትናው ዕለት በደቡብ ኮሪያ የሚገኝ አሜሪካዊ ወታደር ቫይረሱ ተገኝቶበታል።

ወታደሩ ከአሜሪካ ውጪ በቫይረሱ የተያዘው የመጀመሪያው አሜሪካዊ ወታደር ሲሆን በኮሪያ ወረርሽኙ የተከሰተበት አካባቢ የሚገኝ ወታደራዊ ካምፕን ጎብኝቶ እንደነበር ተገልጿል።

በርካታ ደቡብ ኮሪያውያን ወታደሮች ቫይረሱ እንደተገኘባቸውም ማወቅ ተችሏል።

አሜሪካ

ፕሬዝዳንት ትራምፕና ምክትላቸው ማይክ ፔንስ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ኮሮናቫይረስ የአሜሪካ ሕዝብ ላይ የሚደቅነው አደጋ ዝቅ ያለ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ ምክትላቸውን ማይክ ፔንስ መንግሥትን ወክለው ኮሮናቫይረስን እንዲከላከሉላቸው ሾመዋቸዋል።

ተያያዥ ርዕሶች