ትራምፕ ለምክትላቸው ማይክ ፔንስ 'የኮሮና ተከላካይ' ሹመት ሰጧቸው

ዶናልድ ትራምፕና ምክትላቸው ማይክ ፔንስ Image copyright AFP

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ምክትላቸውን ማይክ ፔንስ መንግሥትን ወክለው ኮሮና ቫይረስን እንዲከላከሉላቸው ሾሟቸው።

ትራምፕና ምክትላቸው ፔንስ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ኮሮናቫይረስ የአሜሪካ ሕዝብ ላይ የሚደቅነው አደጋ ዝቅ ያለ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሁለቱ ባለሥልጣናት መግለጫ የሰጡት ኮቪድ-19 የተሰኘ ስያሜ የተሰጠው ኮሮናቫይረስ ከቻይናዋ ዉሃን ግዛት ተነስቶ በዓለም ዙሪያ በፍጥነት መዛመቱን ተከትሎ ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እስካሁን 60 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተዘግቧል። ባለሥልጣናቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ አንድ ግለሰብ በኮሮና መያዙ ተዘግቧል።

በራስ መተማመን የሞላቸው ትራምፕ፤ ዩኤስ ኮሮናቫይረስን የመከላከል ብቃቱ እንዳላት ጠቁመዋል።

«እኛ በጣም፣ በጣም ዝግጁ ነን» ያሉት ትራምፕ አጥኚዎች ለበሽታው ክትባት ለማግኘት ቀን ተሌት እየተጉ እንደሆነ አሳውቀዋል።

ነገር ግን የአሜሪካ ብሔራዊ አለርጂና ተላላፊ በሽታዎች ኃላፊ አንቶኒ ፎኪ የኮሮናቫይረስ ክትባት ቢያንስ በአንድ ዓመት ወይም አንድ ዓመት ተኩል ካልሆነ በቀላሉ እንደማይገኝ ይናገራሉ።

ትራምፕ ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት መገናኛ ብዙሃን ኮሮናቫይረስን አካብደው እያዩት ነው፤ አላስፈላጊ ጩኸት እያሰሙ ነው ሲሉ ትዊተር ገፃቸው ላይ ፅፈዋል።

ቢሆንም ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ አሜሪካ ለቫይረሱ ዝግጁ መሆን አለባት ሲሉ አስጠንቅቀዋል። አልፎም ወደ አንዳንድ ሃገራት የሚደረገው ጉዞ መሰረዙ አግባብ ነው ሲሉ ውሳኔውን አድንቀዋል።

የአሜሪካው ጤና ሚኒስትር አሌክስ አዛር መንግሥታቸው የሚጠበቅበትን ሁሉ እያደረገ እንደሆነ ባይክዱም በአሜሪካ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አልካዱም።