ዓድዋ፡ የቅኝ ግዛት ዘመን ትርክትን የቀየረ ገድል

የአድዋ ድል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአጼ ምኒልክ በተመራው የኢትዮጵያ ሠራዊትና ባህር አቋርጦ ከአውሮፓ ከመጣው የጣሊያን ሠራዊት ጋር የተካሄደው የዓድዋው ጦርነት በታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱ ጉልህ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ አርበኞች የዓድዋ ድል ጣሊያን አፍረካ ውስጥ በተለይ ደግሞ በምሥራቁ የአህጉሪቱ አካባቢ ለማስፋፋት አቅዳ የተነሳችለትን የቅኝ ግዛት ዕቅድን ያጨናገፈ ከመሆኑ ባሻገር፤ በዘመኑ የአውሮፓዊያን ሠራዊት በአፍሪካዊያን ካበድ ሽንፈት ሲገጥመው የመጀመሪያ በመሆኑ ድንጋጤንም ፈጥሮ ነበር።

ለዓደዋው ጦርነት ዋነኛ ምክንያት የሆነው በኢትዮጵያና በጣሊያን መንግሥታት መካከል የተፈረመው የውጫሌ ውል ነበር። በዚህ ውል አንቀጽ 17 ላይ በጣሊያንኛ የሰፈረው ጽሑፍ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በጣሊያ በኩል መሆን እንዳለበት ሲያመለክት የአማርኛው ግን ግንኙነቱን በኢጣሊያ በኩል ማድረግ ትችላለች ይላል።

ይህ የትርጉም ልዩነት እንደታወቀ መጀመሪያ ላይ አጼ ምኒልክ የውሉን አንቀጽ አስራ ሰባት እንደማይቀበሉ ካሳወቁ በኋላ ቀጥሎም የውጫሌውን ውል ሙሉውን ውድቅ አደረጉት። ይህም ጣሊያን ጦሯን በማዝመት ወረራ እንድትፈጽም ሊያደርጋት እንደሚችል የተረዱት ንጉሡ ዝግጅት ማድረግ ጀምረው ነበር።

የተፈራው አልቀረም የጣሊያን ሠራዊት ለወረራ እንቅስቃሴ ጀመረ። ከኢትዮጵያ በኩል የንጉሡን ጥሪ ተከትሎ ከመላዋ አገሪቱ የተሰባሰበው ሠራዊት አገሩን ከጣሊየን ወረራ ለመከላከል ያለውን መሳሪያ ይዞ ወደ ሰሜን አቀና።

በአጼ ምኒልክ የተመራው ሠራዊት እስከ ሃያ ሺህ የሚደርሱ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከአንድ መቶ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አርበኛ ወደ አድዋ ሲተም መነሻው ከአዲስ አበባ ነበር። ሠራዊቱ ዓድዋ ለመድረስ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር አካባቢ በእግሩና በጋማ ከብት መጓዝ ነበረበት።

ሠራዊቱ ዓድዋ ከደረሰ በኋላ ለፍልሚያ አመቺ ጊዜን ሲጠብቅ ቆይቶ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከ17 ሺህ በላይ ወታደሮችን ካሰለፈው አውሮፓዊ ኃይል ጋር ጦርነት ገጠመ።

ጦርነቱ በተጀመረ በግማሽ ቀን ውስጥ የኢትዮጵያ አርበኞች በሁሉም አቅጣጫ በጣሊያን ሠራዊት ላይ በሰነዘሩት ጥቃት ከባድ ጉዳት ስላደረሱበት በአንድ ላይ ተሰልፎ ኢትዮጵያዊያኑን ለመቋቋም ሳይችል ቀረ።

በሺዎች የሚቆጠሩ የጣሊያን ሠራዊት አባላት ሲገደሉ ሌሎች ሺህዎች ደግሞ ተማርከዋል። በዚህም መድፎችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያም ተማርኳል። በተጨማሪም የጣሊያንን ሠራዊት ከመሩት መኮንኖች መካከል ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ሸሽቶ አመለጠ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጦርነቱ ውጤት

የዓድዋ ጦርነት ድል ለጣሊያኖች ሽንፈት አስከትሎ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ከማጽናት ባሻገር ከአድማስ ተሻግሮ አህጉራትን አቋርጦ የተሰማ ጉልህ ተጽዕኖን በዓለም ዙሪያ አስከትሏል።

በዘመናዊው ዓለም የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ ስም ተደጋግሞ ከሚነሳባቸው ክስተቶች መካከል አንዱ ለመሆን ከመብቃቱ ባሻገር በተለይ ደግሞ በጥቁሮች ዘንድ የዓድዋ ድል ለነጻነት በሚያደርጉት ትግል ውስጥ መነቃቃትንና ተስፋን የሰጠ ክስተት ሆኗል።

የዓድዋ ድልን ተከትሎ የታዩ ክስተቶችን በመመልከት የተለያዩ የታሪክ አጥኚዎች የኢትዮጵያዊያን ድል ያስከተለው ውጤት በሚል የሚከተሉትን ነጥቦች አስፍረዋል።

  • አፍሪካን ተቀራምተዋት በነበሩት ቅኝ ገዢዎች ላይ ስጋት ፈጠረ።
  • ዓድዋ አፍሪካ ውስጥ አውሮፓዊያንን የሚገዳደር ወታደራዊ ኃይል እንዳለ አሳይቷል።
  • ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን የኃያልነት ትርክት ከመሰረቱ ቀይሯል።
  • ዓድዋ ኢትዮጵያ ለጥቁሮች የነጻነት ቀንዲል ሆና እንድትታይ አድርጓታል።
  • የጣሊያንን መስፋፋት ቀያሽ የነበረው ፍራንሲስኮ ክርስፒ አስተዳደር እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል።
  • የዓድዋን ጦርነትን የመራው የታላቁን ጀነራል ባራቲየሪ ውድቀት ሆኖ ለሽንፈቱ ክስ ተመስርቶበት ነበር።
  • በመጨረሻም የዓድዋ ጦርነት ምክንያት የነበረውን የውጫሌ ስምምነትን ውድቅ የሚያደርገውና የኢትዮጵያን ነጻ አገርነት የሚቀበለውን የአዲስ አበባ ስምምነትን ጣሊያን እንድትፈርም አደርጓል።