በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ3ሺህ በላይ መድረሱ ተዘገበ

ውሃን ውስጥ ሆስፒታሎች በታማሚዎች ተጨናንቀዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP

ቻይና ተጨማሪ 42 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መሞታቸውን ሪፖርት ማድረጓን ተከትሎ ወረርሽኙ በዓለም ዙሪያ የገደላቸው ሰዎች ቁጥር ከ3 ሺህ ማለፉ ተነገረ።

በበሽታው ከሞቱት ከሦስት ሺህ በላይ ከሚሆኑ ት ሰዎች 90 በመቶ የሚሆኑት በታኅሳስ ወር መብቂያ ገደማ ወረርሽኙ በተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

ከቻይና ቀጥሎ ብዙ ሰዎች በበሽታው የሞቱት ኢራንና ጣሊያን ውስጥ ሲሆን፤ ከ50 በላይ በኢራን ከ30 በላይ ደግሞ ጣሊያን ውስጥ ሞተዋል። በተጨማሪም በሌሎች 10 አገራት ውስጥ ወረርሽኙ የሰዎችን ህይወትን ቀጥፏል።

በዓለም ዙሪያ በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራጨ ሲሆን እስካሁን ድረስ 90 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል። የበሽታው የመዛመት ፍጥነት ከቻይና ይልቅ በተቀረው ዓለም ውስጥ ከፍተኛ ሆኗል።

የዓለም የጤና ድርጅት እንዳለው በወረርሽኙ በተያዙ አብዛኞቹ ሰዎች ላይ የሚታየው ምልክት ቀለል ያለ ሲሆን፤ የሞት መጠኑም በ2 እና በ5 በመቶ መካከል እንደሆነም ተገልጿል።

በአሁኑ ጊዜ የበሽታው መነሻ በሆነችው ቻይና ውስጥ የወረርሽኙ መስፋፋት እየቀነሰ ሲሆን በቀረው ዓለም ግን በሽታው በከፍተኛ ፍጥነት እተዛመተ ነው ተብሏል።

አውሮፓ ውስጥ ወረርሽኙ በስፋት በተገኘባት ጣሊያን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ48 ሠዓታት ውስጥ በእጥፍ መጨመሩን መንግሥት ገልጿል።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 36 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው መረጋገጡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በቁልፍ ጉዳዮች ላይ የሚወስኑትን የመንግሥት ተጠሪዎች ለአስቸኳይ ስብሰባ ዛሬ ጠርተዋል።

ከዚህ ቀደም ተከስተው የነበሩት ሳርስና መርስ የተባሉት የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች አሁን ከተከሰተው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ አንጻር ከፍተኛ የሞት መጠን ነበራቸው ተብሏል።