ሰሜን ኮሪያ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያውን የሚሳኤል ሙከራ አደረገች

ቀደም ሲል የተደረገ የሚሳኤል ሙከራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ቀደም ሲል የተደረገ የሚሳኤል ሙከራ

ሰሜን ኮሪያ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት የመጀመሪያ የሆኑትን ሁለት ዓይነታቸው ያልተለየ ሚሳኤሎችን በመተኮስ ሙከራ ማድረጓ የደቡብ ኮሪያ ሠራዊት አስታወቀ።

ሚሳኤሎቹ ከሰሜን ኮሪያ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ የምሥራቅ ባሕር ተብሎ ወደሚታወቀው የጃፓን ባሕር ከመተኮሳቸው ውጪ በዝርዝር የታወቀ ነገር የለም።

ሰሜን ኮሪያ ለ18 ወራት የሚሳኤል ሙከራ ከማድረግ ተቆጥባ ከቆየች በኋላ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነበር መልሳ የጀመረችው። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ሙከራዎችን ማድረጓ ተነግሯል።

"ሠራዊቱ ተጨማሪ የሚሳኤል ሙከራ የሚኖር ከሆነ በቅርበት እየተከታተለ ሲሆን ለሁሉም ነገር ዝግጁ እንደሆነ ነው" ሲል የደቡብ ኮሪያ ጠቅላይ ኤታማዦር ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ይህ የሚሳኤል ሙከራ የተደረገው ሰሜን ኮሪያ ተቃውሞዋን የገለጸችበትና አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ሊያደርጉት የነበረው ወታደራዊ ልምምድ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ተከትሎ ነው።

በሰሜን ኮሪያና በአሜሪካ መካከል ይደረግ የነበረው ውይይት መቋረጡን ተከትሎ በዚህ የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን አገራቸው አቋርጣው የነበረውን የኑክሌርና የረጀም ርቀት ሚሳኤሎች ሙከራን እንደምትጀምር ተናግረው ነበር።

ኪም "በቅርቡ ዓለም አዲስ ስትራተጂክ የጦር መሳሪያ ያያል" ሲሉ ተናገረውም ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት ሠኔ ወር ላይ በኮሪያ ድንበር ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው ይታወሳል።

ሰሜን ኮሪያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት አሜሪካ ላይ ግፊት ለማሳደር በሚመስል ሁኔታ በርካታ የጦር መሳሪያ ሙከራዎችን አድርጋለች።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ሰሜን ኮሪያ ለምን ኑክሊዬርን መረጠች?