ሶማሊያን የጎበኙ 11 የኬንያ ምክር ቤት አባላት በፖሊስ ምርመራ ተደረገባቸው

የኬንያ ፓርላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አስራ አንድ የኬንያ ፓርላማ የሕዝብ እንደራሴዎች ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ሶማሊያ ውስጥ ካደረጉት ጉብኝት ጋር በተያያዘ በፖሊስ ምርመራ ተደረገባቸው።

በኬንያ የሚገኘው ኤንቲቪ እንደዘገበው የምክር ቤት አባላቱ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ጋር ተገናኝተው አስላማዊውን ታጣቂ ቡድን መቆጣጠር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተወያይተዋል።

ነገር ግን የአገሪቱ የደኅንነት ኃላፊ ሙሪቲ ካንጊ እንዳሉት የምክር ቤት እንደራሴዎቹ ጉብኝት በመንግሥት ይሁንታን ያገኘ አይደለም።

አስራ አንዱ የኬንያ ምክር ቤት አባላት ስለጉዟቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ወደ ሶማሊያ ያቀኑት በግል ፍላጎታቸው እንደሆነ አመልክተዋል።

የቴሌቪዥን ጣቢያው የሕግ አውጪው ምክር ቤት አባላት ከሶማሊያ ጉዟቸው መልስ ናይሮቢ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል በዩቲዩብ ገጹ ላይ አስቀምጧል።

የፓርላማው አባላት ወደ መዲናዋ ናይሮቢ ዋነኛ አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ "ከፖሊስ ጋር ለነበረ ውይይት" ለአጭር ጊዜ ተይዘው የነበረ ሲሆን ነገር ግን ወዲያው ተለቀዋል። በተጨማሪም በቀጣይነት ምንም አይነት ክስ እንደማይመሰረትባቸው ተነግሯል።

ወደ ሶማሊያ በተደረገው ጉዞ ላይ ከተሳተፉት አስራ አንዱ የሕዝብ እንደራሴዎች መካከል አብዛኞቹ ሶማሊያን ከሚያዋስነውና በተደጋጋሚ አልሻባብ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ከሚፈጽምበት የኬንያ ሰሜን ምሥራቅ ግዛት የተወከሉ ናቸው።

በአካባቢው በቅርቡ የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን ከሌሎች የኬንያ ግዛቶች በመምጣት በመንግሥት ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች ስፍራውን ጥለው ሸሸተዋል።