ኢትዮጵያ ውስጥ የቀለጡት አርመኖች ታሪክ

ኢትዮጵያ ውስጥ የቀለጡት አርመኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጋዜጠኛ ኢስማኤል ኢናሼ ኢትዮጵያ ስለሚኖሩ አርመኖች ለማወቅ ጉዞ ጀምሯል - ፍለጋውን የጀመረው ደግሞ ከአዲስ አበባ እምብርት ፒያሳ ላይ ነው።

ከዚህ ቀደም ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ አርመኖች በብዛት እንደሚኖሩ ጭምጭምታ ሰምቷል፤ ታሪካቸውንም ማንበብ ችሏል።

ኢትዮጵያና አርሜኒያ በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አማካይነት ለዘመናት የዘለቀ ግንኙነት አላቸው። ከዚያም አልፎ ዲፕሎማቶችና ነጋዴዎች ከአንዷ አገር ወደ አንዷ አገር ይመላለሳሉ።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን በጣት የሚቆጠሩ አርመናዊያን በምኒሊክ ቤተ-መንግሥት ፍርድ ቤት ውስጥ ሚና ነበራቸው። 20ኛው ክፍለ ዘመን ከገባ በኋላ የአርመን ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተመ። የአርመኖች ምጣኔ ሃብታዊ ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም።

በአንድ ሞቃታማ ከሰዓት ኢስማኢል ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የአርመን ቤተክርስትያን ያመራል። ቤተ-እምነቱ በ1930ዎቹ የተገነባ ነው።

ዝግ ቢመስልም 'ሰላም' ሲል ድምፁን ያሰማል። አንድ ግራ የገባቸው የሚመስሉ ሸምገል ያሉ ሰው ወደ በሩ ይመጣሉ። ኢስማኢል ወደ ውስጥ ዘልቄ ማየት እፈልጋለሁ ይላቸዋል። 'ቆይ ጠብቅ' ይሉና ሳይመንን ይጠሩታል።

ሳይመን ኢትዮጵያዊ አርመናዊ የቤተ-ክርስትያኗ ተንከባካቢ ነው።

የኃይለሥላሤ ተፅዕኖ

ቤተ-መቅደሱ በቀይ ምንጣፍ የደመቀ ነው። ቤተ-እምነቱ አልፎ አልፎ ነው የሚከፈተው። ምክንያቱም ብዙ የአርመን ቄሶች የሉም። አባላቱም ቢሆኑ ከ100 አይበልጡም። አብዛኛዎቹ ደግሞ ዕድሜያቸው የገፋ ነው።

በቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ዘመነ መንግሥት አርመኖች አዲስ አበባን ወረዋት ነበር። በቁጥር እጅግ የላቁ ነበሩ። ቀ.ኃ.ሥ. ሃገራቸውን ማዘመን በመሻታቸው አርመናዊያን የፍርድ አማካሪዎችንና ነጋዴዎችን አስመጡ። እኒህ አርመናዊያን አዲስ አበባን ስትዘምን የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል።

ልዑል ራስ ተፈሪ፤ እየሩሳሌም የሚገኘውን የአርመን ገደም የጎበኙት በ1916 ነበር። በወቅቱ በኦቶማን ቱርክ ወታደሮች ወላጆቻቸው የተጨፈጨፉ 40 ገደማ አርመናዊያን ሕፃናትን ጎብኝተውም ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይሄኔ ራስ ተፈሪ፤ የገዳሙን ጳጳስ 40ዎቹን ልጆች ወስደው ኢትዮጵያ ማሳደግ ይችሉ እንደሆን ይጠይቋቸዋል። ይሁንታንም ያገኛሉ። በተለምዶ 40ዎቹ ልጆች የሚባሉት አርመናዊያን ሙዚቃ የተማሩ ስለነበሩ ኢትዮጵያ ሲመጡ ንጉሣዊ ብራስ ባንድ ይመሠርታሉ።

መቼም ብዙዎቻችን ኬቮርክ ናልባንዲያንን አንዘነጋቸውም። የንጉሡ ዘመን ኢትዮጵያን ብሔራዊ መዝሙር የሠሩት እሳቸው ነበሩና።

በ1960ዎቹ 1200 ገደማ አርመናዊያን አዲስ አበባ ይኖሩ እንደነበር ይታመናል። ምንም እንኳ ቁጥራቸው ያነሰ ቢሆንም የነበራቸው ተፅዕኖ ላቅ ያለ ነበር። የኢትዮጵያን ጃዝ ሙዚቃ ከመቃኘት ጀምሮ ልብስ ሰፊ፣ ዶክተር፣ ነጋዴ ሆነው በመዘናዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ውስጥ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል።

ድኅረ-ቀ.ኃ.ሥ.

የአርመን ማኅበረሰብ ከንጉሡ ጋር የነበራቸው ቁርኝት ጠበቅ ያለ ስለነበር ንጉሡ ከሥልጣን ሲወርዱ የአርመኖች ቁጥር ማሽቆልቆል ጀመረ።

ኃይለሥላሤ በ1966 በማርክሲስቱ ደርግ ከሥልጣን ተወገዱ። ወታደራዊው መንግሥት የግል መኖሪያዎችንና ንግድ ቤቶችን የመንግሥት ማድረግ ጀመረ። በርካታ አርመናዊያንም ቤት ንብረታቸውን ተቀሙ። ይህን ተከትሎ ብዙዎች ወደ ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ኮበለሉ።

ጥቂቶች ግን ትዳር አድርገው፤ ቤተሰብ መሥርተው መኖር ጀመሩ።

አልፎ አልፎ ቤተክርስትያኗ ዝግጅት ሲኖራት ይመጣሉ።

ጣት የሚያስቆረጥም

አርመኖች አንድ ማኅበራዊ ክለብ አላቸው። ክለቡ ሬስቶራንት አለው። አገር ቤት አገር ቤት የሚሸት ምግብ ይከሽናል። ኢስማኢል እዚህ ሬስቶራንት ሄዶ የአርመን ምግብ እንዲሞክር ሳይመን ይነግረዋል።

አንድ ማክሰኞ ምሽት ኢስማኢል ጓደኛውን ይዞ ወደ ሬስቶራንቱ ያቀናል። አርመናዊ ኢትዮጵያዊያን ጥግ ጥግ ይዘው ይመገባሉ። ፀጉረ ልውጥ በማየታቸው ደስ ተሰኝተዋል።

የአርመን ማኅበረሰብ እንዲህ እንደአሁኑ ሳይከስም በፊት ቦታው ደማቅ ነበር ይላሉ። ነገር ግን ማኅበራዊ ክለቡ የቀሩትን አርመኖች ለማስተሳሰር ይረዳል ይላሉ።

ኢስማኢል ቦረክ እና ልዩላ ከባብ የተሰኙትን የአርመን ምግቦች እየጠቀለለ ይጎርሳል። 'የአርመኖችን ታሪክ በኢትዮጵያ አጣጣምኩት' ያለው ወዶም አይደል።