ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጉልበታቸውን እየገበሩ ያሉት የቻይና ሙስሊሞች

ለዓለም ኩባንያዎች ጉልበታቸውን እየገበሩ ያሉት የቻይና ሙስሊሞች

በሺዎች የሚቆጠሩ የቻይና ዩገር ሙስሊሞች በጣም በአስቸጋሪ ሁኔታ ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጉልበታቸውን እየገበሩ ነው ሲል እንድ ሪፖርት ይፋ አደረገ።

የአውስትራሊያ ስትራቴጂክ ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ቻይና ሙስሊም ዜጎቿን ማስተማር በሚል የጉልበት ብዝበዛ እያካሄደች ነው።

አንድ ሚሊዮን ገደማ ሙስሊሞችን ቻይና በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ አስገብታ ሐይማኖታቸውን እንዲተዉ እየቀጣች ነው ተብላ ትወቀሳለች። የቻይና ባለሥልጣናት ግን ካምፖቹ አክራሪነትን ለመዋጋት የተለሙ ናቸው ይላሉ።

ባለፈው ታኅሣስ የቻይና ባለሥልጣናት ማጎሪያ ካምፖቹ ውስጥ ያሉ በርካታ ሙስሊሞች 'ተመርቀዋል' ሲሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር።

እንደ ኢንስቲቲዩቱ ዘገባ እንደ በአውሮፓዊያኑ ከ2017-2019 ባለው ጊዜ 80 ሺህ ገደማ የዩገር ሙስሊሞች በአገሪቱ በሚገኙ ትላልቅ ፋብሪካዎች እንዲያገለግሉ ተሰማርተዋል። ይህ የተደረገው ደግሞ ዢንዢያንግ ኤይድ በተሰኘ የመንግሥት የአሠሪና ሠራተኛ ፖሊሲ አማካይነት ነው።

ዘገባው የዩገር ሙስሊሞች ይህንን 'ሲስተም' ሊያመልጡ በፍፁም እንደማይቻላቸው፤ አንቀበለውም ቢሉ ደግሞ መጨረሻቸው ማጎሪያ ካምፕ እንደሆነ ይተነትናል።

ኢንስቲቲዩቱ የወረዳ ባለሥልጣናትና ደላላዎች በእያንዳንዱ የዩገር ሙስሊም ከመንግሥት ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ጨምሮ ያስረዳል።

ቻይና ቁጥራቸው በርከት ያለ ሙስሊም ዜጎቿን ወደ ማጎሪያ ካምፕ እየወሰደች እንደሆነ መረጃ መውጣት የጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር። የቻይና ባለሥልጣናት ግን ካምፖቹ ቴክኒክና ሙያ መማሪያ ናቸው ሲሉ አስተባብዋል።

ነገር ግን የሚወጡ ዘገባዎች የዩገር ማኅበረሰብ አባላት እምነታቸውን በመግለፃቸው ብቻ እየታጎሩ እንደሆነ ማሳየት ጀምረዋል።

ቻይና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ቢደርስባትም የጉልበት ሠራተኞቹ በፍቃዳቸው ነው የሚንቀሳቁት ስትል በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣብያዋ አሳወቀች።

የአውስትራሊያው ድርጅት እንደሚለው ናይክ፣ አፕልና ዴል የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች ውስጥ የቻይና ሙስሊሞች ይሠራሉ። የሚኖሩትም በሚጠበቅ ግቢ ውስጥ ነው።

ዓለም አቀፍ ኩባንያዎቹ ግን በዓለም ሕግ መሠረት እየተዳደርን ነው ይላሉ። የተጣሰ ሕግ ካለም እናጣራለን የሚል መልዕክት ያስተላልፋሉ።