ጊኒ ቢሳው፡ በሞት ማስፈራራት ዛቻ ለአንድ ቀን ብቻ በስልጣን የቆዩት ፕሬዚዳንት

ሲፕሪያኖ ካሳማ

የፎቶው ባለመብት, Dan Sanha

በጊኒ ቢሳው አወዛጋቢውን ምርጫ ተከትሎ ሁለት ፕሬዚዳንቶች አገሪቷን እንዲመሩ ቢወሰንም አንደኛው ፕሬዚዳንት ሲፕሪያኖ ካሳማ ከአንድ ቀን የስልጣን ቆይታ በኋላ ራሳቸውን አግልለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከስልጣናቸው ለአንድ ቀን ብቻ እንዲቆዩ ያስገደዳቸው ምክንያት የሞት ማስፈራሪያ ዛቻ ስለደረሳቸው ሲሆን "ለህይወቴም ያሰጋኛል" ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ሲፕሪያኖ ካሳማ የተመረጡት በህግ አውጭው አካል ሲሆን ይህም በአገሪቷ ተደርጎ የነበረውን የታህሳሱን ምርጫ ተከትሎ ነው።

ቢሆንም ሌላኛው ፕሬዚዳንት የጦር አበጋዙ ኡማሮ ሲሶኮ ኤምባሎ በመዲናዋ ቢሳው የፕሬዚዳንትነት ቃለ መሓላቸውን ፈፅመዋል።

የአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ኡማሮ ኤምባሎ ተቀናቃኛቸውን ዶሚንጎስ ሲሞስ ፔሬራ 54 ለ46 በመቶ ድምፅ አሸንፈዋል በማለት አውጆ ነበር።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆሴ ማሪዮ ቫዝ ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ኡማሮ ኤምባሎ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በነበረ ስነ ስርአት ስልጣናቸውን አስረክበዋል።

ነገር ግን ተቀናቃኛቸውና ጊኒ ቢሳውን ወደ ነፃነት ያሸጋገሯት ሲሞስ ፔሬራ የስልጣን ርክክቡን አልቀበልም ብለዋል፤ ምክንያቱም የአሸናፊው ፓርቲ ህጋዊነት የለውም በማለት ምርጫው ከፍተኛ ማጭበርበር የነበረበት ነው ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስኪወስን ድረስ የፓርላማ ቃል አቀባዩ ሲፒሪያኖ ካሳማ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ሾሟቸው ነበር።

ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን መልቀቃቸውንም ተከትሎ የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ተዘግተዋል፤ በከፍተኛ ጦር መሳሪያዎች ተከበዋል።

በአገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ ሊከተል እንደሚችል እየተጠቆመ ሲሆን፤ አንዳንድ የፓርላማ አባላት መፈንቅለ መንግሥትም እንዲካሄድ ጥሪ እያደረጉ ነው።

ከጎርጎሳውያኑ 1980 ጀምሮ በጊኒ ቢሳው ዘጠኝ መፈንቅለ መንግሥቶች ተካሂደዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images