ሳዑዲ አረቢያ፡ አረብ አገር የለፋችበትን አገባሻለሁ ባለሰው ተጭበርብራ ባዶዋን የቀረችው ሻሼ

የፎቶው ባለመብት, SHASHE
ህይወታቸውን ለመቀየር ከአገራቸው ውጪ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሴት ኢትዮጵያዊያን ለቀጣይ ዕቅዳቸው ማሳኪያ የቆጠቡት ገንዘብ በፍቅር ጓደኞቻቸው አሊያም በቤተሰብ አባላቸው ተወስዶ ወይም ባክኖ ባዷቸውን ቀሩ ሲባል መስማት እየተለመደ የመጣ ነገር ሆኗል።
በተለይ በአረብ አገራት ውስጥ ህይወታቸውንና ጤናቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ ከባድ ሁኔታ ውስጥ በመሥራት ወደ አገራቸው ሲመለሱ የራሳቸውን ሥራና ህይወት ለመመስረት ያስችለናል ያሉት ገንዘብ ጠፍቶ ወይም ባክኖ ሲያገኙት የሚፈጠርባቸው ስሜት ከባድ ከመሆን አልፎ አንዳንዶችንም ለሥነ ልቦና ጫና እንደዳረጋቸው የሚሰሙ ታሪኮች ይጠቁማሉ።
በውጪ አገር ሰርተው ያጠራቀሙትና ወደ አገር ቤት የላኩት ገንዘብ ባመኑት ሰው ከተበላባቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን እህቶች መካከል ሻሼ አንዷ ናት።
ሻሼ፤ የተወለደችው በምዕራብ ሸዋ ኮቲቤ በምትባል አካባቢ ነው። ሳዑዲ የምትኖረው ሻሼ በትውልድ ቀዬዋ ከሚኖር ከአንድ ግለሰብ ጋር ወደ አገሯ ስትመለስ ለመጋባት አቅደው ለወደፊት ህይወታቸው የሚሆኑ ነገሮችን እንዲያሟላ የላከችለትን ገንዘብ እንዳጭበረበራት ትናገራለች።
ሙሉ ታሪኳን እነሆ . . .
ሻሼ ለሥራ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ነበር የሄደችው «ሳዑዲ አራቢያ ከሄድኩ በኋላ የቀጠረቻት ሴት እህት መንቀሳቀስ አትችልም። የምትበላው የምትጸዳዳውም በተኛችበት ነበር። ልብሷን መቀየር፣ ማጽዳትም የዘወትር ሥራዬ ነበር» ትላለች።
ሻሼ፤ ለአራት ዓመት እሷን ስትንከባከብ በወር የሚከፈላት 700 ሪያል የነበረ ሲሆን ደመወዟ ደግሞ በጊዜ አይሰጣትም ነበር።
«ብዙ መከራ አሳልፌ ከዚያ ቤት ወጥቼ ሌላ ቤት በ900 ሪያል ተቀጠርኩ።»
«አዲስ የገባሁበት ቤት ተቆልፎብኝ ይውላል፣ ያድራል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ለሁለት ዓመት ቆየሁ። ለ24 ሰዓታት ስለሚቆለፍብኝ፣ መስኮትም ስለማይከፈት ፀሐይ መውጣትና መግባቷን እንኳ አላውቅም ነበር።»
ሻሼ፤ በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ ሰውነቷ ተጎድቶ እንደነበርም ትናገራለች። ከተቀጠረችበት ቤት ሥራ ስትጨርስ ቀጣሪዋ እህት ቤት ተወስዳ ደግሞ ሌላ ሥራ እንደትሰራ ትደረግ ነበር። በዚህ መልኩ እየሰራች ለስድስት ዓመት ያገኘችውን ብር ለማጠራቀም ሞክራለች።
ሻሼ ሳዑዲ ውስጥ በከባድ የቤት ውስጥ ሥራ ዓመታትን ካሳለፈች በኋላ ወደ አገሯ ተመልሳ የምታሳካው ዕቅድ እንደነበራት ትናገራለች።
«አገር ቤት ፍቅረኛ ነበረኝና ስመለስ ለመጋባት ተስማምተን ነበር። ስልክ ስላልነበረኝ የምደውልለት ከአሰሪዬ ስልክ እየለመንኩ ነበር። አሰሪዎቼን ከፍቅረኛዬ ጋር ለመጋባት ወደ አገር ቤት ስለምሄድ ስልክ ግዙልኝ ብዬ ለመንኳቸው።»
አሰሪዎቿ ስልክ ከገዙላት በኋላ ኢሞ የተሰኘ መደዋወያ ስልኳ ላይ ትጭናለች። ከዚያም በአንድ አጋጣሚ አንድ የተወለደችበት አካባቢ እንደሆነና በስም የምታውቀው ልጅ ስልክ ይደውልላታል።
ቢሆንም ግን ከልጁ ጋር በአካል አይተዋወቁም ነበር። ከቤተሰቦቿ ጋር ቅርበት ያለው የግለሰቡ ወንድም ደውሎ ልጁ የቤተክርስቲያን አገልጋይና መልካም ሰው እንደሆነ በመግለፅ እንድታገባው ሃሳብ ሰነዘረላት።
«ፍቅረኛ እንዳለኝ ነገርኩት። ማነው ሲለኝ የፍቅረኛዬን ሙሉ ስም ነገርኩት። 'እሱማ ወለጋ ሄዶ አግብቶ ሚስቱን ትቶ እዚህ ተመልሷል። እዚህም አግብቶ ሁለት ልጅ ወልዷል' አለኝ። 'በሰው አገር ይህን ያህል ለፍተሽ ያገኘሽውን ብር ባገባ ሰው ላይ ማጥፋት የለብሽም' አለኝ። በፍቅረኛዬ በጣም አዘንኩ። ከዚያ ከአዲሱ ጓደኛዬ ጋር ተቀራረብንና ለመጋባት ተስማማን።»
ጓደኛዋ፤ ቤት ሰርቶ እንዲጠብቃት መሬት መግዣ ብር እንድትልክለት ይጠይቃታል። 'የእግዚአብሔር ሰው ስለሆንኩ ብርሽን አልበላም' ሲልም ቃለ ገባ።
እሷም መልካም ሰው ነው ብላ ብዙ ደክማ የቆጠበችውን ብር ሙሉ በሙሉ ላከችለት። መጀመሪያ 10 ሺህ ሪያል በባንክ አስገባች። ከዚህ በኋላ እሱ ደግሞ መሬት እንደገዛ ነገራት። ትንሽ ቆይቶ መንግሥት መሬቱን ወስዶብኝ ነበር አሁን ግን መልሶልኛል እንዳላትም ታስታውሳለች።
በማስከተል ደግሞ መንግሥት መሬቱን መልሶ እንዳይወስደው በሽቦ ለማጠር ብር ላኪልኝ አላት። እሷም እጇ ላይ የነበረ ብር ላይ ከቀጣዩ ወር ደመወዟ ተበድራ በመጨመር 4500 ሪያል ላከችለት። ከዚህ ቀጥሎ የሆነው ግን ፈፅሞ ያልጠበቀችው ነበር።
«እሁድ ልኬለት ሰኞ ደረሰ ወይ ብዬ ስደውልለት 'ብሎክ' አድርጎኛል። ደጋግሜ ብሞክርም ላገኘው አልቻልኩም»
«ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ራሴን አላውቅም። ለሦስት ወር ያህል ምግብ በአግባቡ አልበላም ነበር። ደም በአፍና አፍንጫዬ ይወጣል። በቀን ሦስቴ ሆስፒታል ሄጄ 'ግሉኮስ' እየወሰድኩ ወደስራ እመለሳለሁ። ስድስት ዓመት የሰራሁበትን በሙሉ አጥቻለሁ» ትላላች ፍጹም በተሰበረ ሁኔታ።
ሻሼ በኋላ ላይ እንደደረሰችበት የቀድሞ ፍቅረኛዋ እንዳላገባ ሰማች፤ ይህም ሃዘኗን የበለጠ አጠነከረባት።
ሻሼ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሄደችው አባትና እናቷ በተመሳሳይ ጊዜ በሞት በተለይዋት ወቅት ስለነበረ «በከባድ ሃዘን ተሰብሬ ነበር» ትላለች። ስለዚህም የምትሰራው ከባድ የቤት ውስጥ ሥራ ሃዘኗ የበለጠ አጠንክሮባት የነበረ ሲሆን አብሯት ለረጅም ጊዜ ቆይቷል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና ያጠራቀመችው ገንዘቧ የወደፊት የህይወት አጋሬ ይሆናል ባለችው ግለሰብ ስትጭበረበር የገጠማት መረበሽ ተስፋ እስከመቁረጥ እንዳደረሳት «ሃዘኑ፣ የሥራ ጫናውና መጭበርበሬ በአንድ ላይ ተደማምሮ ራሴን ስለማጥፋት ሁሉ አስብ ነበር» ትላለች።
ከዚህ ሁሉ በኋላ የሻሼ ወንድም በእህቱ ላይ የተፈጸመውን ማጭበርበር ለፖሊስ ቢያመለክትም ያጭበረበራት ግለሰብ ገዛው የተባለውን መሬት ሸጦ ከአካባቢው መሰወሩን ፖሊስ እንደገለጸለት ትናገራለች።
ሻሼ የወደፊት ህይወቷን ለማሳካት ስድስት ዓመታትን ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በከባድ የቤት ውስጥ ሥራ አሳልፋለች፤ ይህም ሳያንስ ባርነት በሚመስል ልፋት ያጠራቀመችው ገንዘቧ የህይወት አጋሬ በመሆን ሸክሜን ያቀልልኛል ባለችው ግለሰብ ተጭበርበርራ ባዶ እጇን ቀርታለች። ዙሪያዋም ገደል ሆኖባታል።