ኮሮናቫይረስ፡ ቫይረሱ የአእምሮ መረበሽን እያስከተለ ነው ተባለ

ኮሮናቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, yonhap/AFP

በቻይናዋ ሆንግ ኮንግ ከተማ ኮሮናቫይረስ ጥቂት በማይባሉ ሰዎች ላይ የአእምሮ መቃወስን እያስከተለ እንዳለ የሮይተርስ ዘገባ አመለከተ።

በሆንክ ኮንግ እስካሁን መቶ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ሁለት ደግሞ በቫይረሱ መሞታቸው ተመዝግቧል።

ነገር ግን እንደ አውሮፓውያኑ በ2003 በግዛቲቱ ሳርስ 300 የሚሆኑ ሰዎችን የመግደሉን እውነታ በማስታወስ የሆንግ ኮንግ ኗሪዎች ዛሬም ያ ታሪክ ሊደገም ይሆን በሚል ከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸው እየተነገረ ነው።

ኮሮናቫይረስ መከሰትን ተከትሎ በሆንግ ኮንግ እየተስተዋለ ያለውን ጭንቀትና ውጥረት መነሻ አድርጎ ጥናት የሰራው የሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑ የከተማዋ አዋቂ ሰዎች የአእምሮ መረበሽ ሲያጋጥማቸው 11 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ድብርት ውስጥ መግባታቸውን አረጋግጧል።

በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ስራቸውን ከቤት ሆነው እየሰሩ ሲሆን ምግብ እና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮች በቤት ውስጥ ማከማቸትም የከተማዋ ነዋሪ መሰረታዊ ተግባር ሆኗል።

የፊት ጭምብልና የእጅ ንፅህና መጠበቂያዎች ደግሞ ለረዥም ጊዜ የአቅርቦት ችግር ነበር።

በቻይና ዛሬ ማክሰኞ እለት 125 የኮሮናቫይረስ ኬዞች የተመዘገቡ ሲሆን ይህ ቁጥር ባለፉት ስድስት ሳምንታት ከተመዘገቡ አዳዲስ የለት 'ተለት ስርጭቶች ዝቅተኛ የሚባል ነው ተብሏል።

ቫይረሱ በተቀሰቀሰባት ሁቤይ ግዛት 31 ተጨማሪ ሞቶች ሲመዘገቡ በጥቅሉ በቻይና 2943 ሰዎች በኮሮናቫይስ ሞተዋል።

በሌላ በኩል ቫይረሱ ተመልሶ እንዳይመጣ በማሰብ የቻይናዋ ጉዋንዶንግ ግዛት ቫይረሱ ከተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች ለ14 ቀናት ራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩ አስታውቋል።

የግዛቲቱ ባለስልጣናት፤ በዚህ መልኩ ራሳቸውን ማግለል ያለባቸው ከየት አገር የሚሄዱ ሰዎች እንደሆኑ አገራትን ለይተው አላስቀመጡም።