ኮሮናቫይረስ፡ ትዊተር በቫይረሱ ምክንያት ሠራተኞቹ ከቤታቸው እንዲሠሩ ፈቀደ

ትዊተር በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሠራተኞቹ ከቤት እንዲሠሩ ፈቀዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ትዊተር የተሰኘው ግዙፍ የማሕበራዊ ሚድያ ኩባንያ ሠራተኞቹ ኮሮናቫይረስ እንዳይዛቸው በመስጋት ከመኖሪያ ቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ድርጅቱ በድረ-ገፅ እንዳሳወቀው ሆንግ ኮንግ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ የሚገኙ ሠራተኞቹ በጠቅላላ ከቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ ተፈቅዶላቸዋል።

ከእነዚህ ሃገራት አልፎ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ 5 ሺህ ሠራተኞች ከመኖሪያቸው ሆነው እንዲሠሩ እያበረታታ መሆኑ ተሰምቷል።

ድርጅቱ ከጥቂት ቀናት በፊት በጣም አስፈላጊ ካልሆነ ሠራተኞቹ በፍፁም ጉዞ እንዳያደርጉ እንዲሁም አላስፈላጊ ዝግጅቶች እንዲቀሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ትዊተር፤ ሂዩስተን ቴክሳስ ውስጥ ሊካሄድ የታሰበ የሚድያ ኮንፈረንስ ላይ እንደማይሳተፍ ማሳወቁ አይዘነጋም።

የድርጅቱ ሰው ኃይል አስተዳዳሪ ጄኒፈር ክሪስቲ "ዓላማችን ኮሮናቫይረስ በሠራተኞቻችን መካከል የሚሠራጭበት ፍጥነትን መግታት ነው። አልፎም የሠራተኞቻችንን ቤተሰቦች መታደግ ነው" ሲሉ ውሳኔያቸውን አስረግጠዋል።

የትዊተር አለቃ ጃክ ዶርሲ ከኮሮናቫይረስ መከሰት በፊት ጀምሮ ከቤት መሥራት አዋጭ ነው ብሎ እንደሚያምን ይነገርለታል። ባለፈው ጥቅምት ለስድስት ወራት ያክል አፍሪካ ውስጥ መኖር እፈልጋለሁ ሲልም አስታውቆ ነበር።

እስያ ውስጥ ያሉ በርካታ ኩባንያዎች ተመሳሳይ መርህ እየተከተሉ ነው። የቫይረሱ ሥርጭት ያሰጋቸው የትየለሌ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

አልፎም ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በዚህ ዓመት የሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ እንደማይሳተፉ እያሳወቁ ነው። ሠራተኞቻቸው ከሃገር ሃገር የሚያደርጉትን ጉዞ ገታ እንዲያደርጉም አሳስበዋል። በዚህ ፌስቡክና እና ጉግል ተጠቃሽ ናቸው።

በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሶስት ሺህ በላይ መድረሱ ተሰምቷል።