በኮሮናቫይረስ ፍራቻ በእግር ሰላምታ የሰጡት ፕሬዚዳንት

የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ

የፎቶው ባለመብት, Tanzania's State House

ከሰሞኑ የዓለምን ልብ ሰቅዞ የያዘውና ለብዙ ሺዎች ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው የኮሮናቫይረስ መዛመት ነው። ከሃዘኑና ከፍራቻውም ጋር ተያይዞ አንዳንድ አስገራሚ ዜናዎችም እየተሰሙ ነው።

በዛሬው እለትም የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ከተቀናቃኛቸው ማሊም ሰይፍ ሸሪፍ ሐማድ ጋር እንደተለመደው በእጅ ሳይሆን በእግራቸው ለሰላምታ ሲጨባበጡ የሚያሳየው ፎቶ በፅህፈት ቤታቸው በኩል ወጥቶ ብዙዎችን አስደምሟል።

የእጅ ሰላምታን ያስወገዱበትም ምክንያት በኮሮና ቫይረስ ፍራቻ መሆኑም ተገልጿል። የአገሪቱ የጤና ሚኒስትርም የኮሮናቫይረስን ለመከላከል መወሰድ ከሚገባቸው እርምጃዎች መካከል የእጅ ንክኪ ማስወገድ አንዱ ነው ማለቱን ተከትሎ ነው ፕሬዚዳንቱ ይህንን ተግባራዊ እያደረጉ ያሉት።

እስካሁን ባለው መረጃ 3ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት የሞቱ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለውም ሟች የሚገኘው የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ዉሃን ከተማ ነው።

አብዛኛው ሞት እየተከሰተ ያለው በቻይና ቢሆንም በባለፉት ሁለት ቀናት ግን በሌሎች አገሮች ያለው የቫይረሱ መዛመት በዘጠኝ እጥፍ ጨምሯል ተብሏል።

የተለያዩ አገራት የቫይረሱን መዛመት ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ሲሆን፤ ታንዛንያን ጨምሮ በመላው ዓለም ያሉ መንግሥታት ማንኛውንም ንክኪ ዜጎቻቸው እንዲያስወግዱ እየመከሩ ነው።

መሳሳም፣ መተቃቀፍ እንዲሁም ማንኛውንም የእጅ ሰላምታ እባካችሁ አስወግዱ በማለት እየተማፀኑ ነው።

ታንዛንያ ውስጥ እስካሁን በቫይረሱ የተያዘ ሰው ባይኖርም በአፍሪካ ውስጥ በግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል ቫይረሱ የያዛቸው ሰዎች መኖራቸው ተረጋግጧል።