ቴድሮስ አድሃኖም፡ ከኮሮናቫይረስ ጋር የሚደረገውን ፍልሚያ የሚመሩት ኢትዮጵያዊ

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኮሮናቫይረስ ዓለምን ሰቅዞ በያዘበት ወቅት የዓለም የጤና ድርጅት ኃላፊ መሆን ምን ያህል ፈታኝ ሥራ ይሆን?

በየቀኑ ጄኔቫ ከሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። የቫይረሱ ተያዦች ቁጥር በየቀኑ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይስተዋልም።

ኢትዮጵያዊው ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ [ፒኤችዲ]፤ የመጀመሪያው አፍሪካዊ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ናቸው። የዛሬ ሁለት ዓመት ተኩል ገደማ ነው ሃላፊነቱን የተረከቡት።

በየዓመቱ ሚሊዮኖችን እየገደሉ ያሉ እንደ ወባ፣ ኩፍኝና ኤድስን እገታለሁ ሲሉ ነበር በወቅቱ ቃል የገቡት። ምንም እንኳ መሥሪያ ቤታቸው እነዚህን በሽታዎች ለመግታት ቢታገልም፤ በሥልጣናቸው መባቻ ከባድ ፈተና ሆኖባቸው የነበረው ኮንጎ ውስጥ የተቀሰቀሰው ኢቦላ ነበር።

አሁን ደግሞ ኮሮናቫይረስ።

ሁለቱም በሽታዎች አስቸኳይ እርዳታ የሚሹ በሽታዎች ተብለው ታውጀዋል። ይህ ማለት 24 ሰዓት ክትትል ማድረግ፤ ባለሙያዎችን ማሠራጨት፤ በበሽታው ከተጠቁ ሃገራት ጋር መነጋገር እና መረጃዎችን ለዓለም ሕዝብ ማድረስን ይጠይቃል።

ሞገስ ያለውና የተረጋጋ

ሰውዬውን በቅርበት የሚያውቋቸው 'ሞገስ ያለውና የተረጋጋ ነው' ሲሉ የ55 ዓመቱን ጎልማሳ ዶ/ር ቴድሮስን ይገልጿቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ሆነው እንደተመረጡ በሰጡት የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫቸው የጄኔቫ ጋዜጠኞች ግራ ተጋብተው ነበር። ፈገግና ረጋ ብለው ተቀምጠው ዝቅ ባለ ድምፅ ነበር መግለጫ ሲሰጡ የነበሩት። ቢሆንም ለቦታው የተሰጡ ሰው መሆናቸውን ብዙዎች ተረድተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በኢትዮጵያ በመንግሥት ኃላፊነት አገልግለዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ነበሩ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነውም አገልግለዋል።

'ወንድሜን የገደለው ኩፍኝ ሳይሆን አይቀርም'

ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ ሳሉ በኤርትራ ክፍለ ግዛት አስመራ ከተማ ነበር የተወለዱት። ጊዜው ደግሞ 1958 ዓ.ም ነበር፤ ዕድገታቸው ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል።

ወንድማቸው ገና የአራት ዓመት ሕፃን ሳለ በያዘው በሽታ ሞተ። ዶ/ር ቴዎድሮስ ወደ ጤና ትምህርት እንዲያጋድሉ ያደረጋቸው ይህ እንደሆነ ይናገራሉ። "ተማሪ እያለሁ ነበር ወንድሜን የገደለው ኩፍኝ ሳይሆን እንዳልቀረ የገመትኩት" ብለዋል ታይም ከተሰኘው መፅሔት ጋር በነበራቸው ቆይታ።

"የዛኔም አልተቀበልኩትም፤ አሁን አልቀበለውም" የሚሉት ኃላፊው ሕፃናት መዳን በሚችል በሽታ መሞት የለባቸውም የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው። "ሁሉም መንገዶች ወደ ዓለም አቀፍ የጤና ሽፋን ማምራት አለባቸው። ይህ እውን ሳይሆን የሰላም እንቅልፍ አልተኛም" ሲሉ ከመመረጣቸው በፊት የተናገሩት አይረሳም።

ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ሚኒስትር እያሉ በዘርፉ ብዙ ለውጦች አምጥተዋል ተብለው ይሞገሳሉ። በተለይ ደግሞ የጤና ሽፋንን በማዳረስ በኩል 'የሚያስጨበጭብ' ሥራ ሠርተዋል።

ነገር ግን በሳቸው የሚኒስትርነት ዘመን ጋዜጠኞች ስለ ኮሌራ እንዲዘግቡ አይበራታቱም ነበር የሚል ወቀሳም ይነሳባቸዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት ያሉበትን እክሎች እንዲወጣ ከ194 አባል ሃገራት ጋር ተባብሮ መሥራ እንዳለበት ጠንቅቀው ያውቃሉ። ለዚህም ይመስላል በኢቦላ ወረርሽኝ ወቅት ከአንድም ሁለት ሶስቴ ወደ ሥፍራው የተጓዙት። የኮሮናቫይረስ ጉዳይ ሲሰማም ወደ ቤይዢንግ ለመብረር የቀደማቸው አልነበረም።

የጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ሎውረንስ ጎስቲን "ወደ ቻይና የሄዱት መንግሥት ስለበሽታው ግልፅ የሆነ መረጃ እንዲሰጥና ከዓለም ጤና ድርትጅ ጋር እንዲተባበር ነው። የቻይና መንግሥትን መውቀስ አማራጭ እንዳልሆነ ያውቁታል" ይላሉ።

የቻይና ነገር

አንዳንድ የዓለም ጤና ድርጅትን እንቅስቃሴ በንቃት የሚከታተሉ ሰዎች ኃላፊው የቻይና መንግሥትን ማሞጋገሱ ተገቢ አይደለም ባይ ናቸው።

ዶ/ር ቴዎድሮስ ቤይዢንግ እንደደረሱ የቻይና መንግሥት "ወረርሽኝን በመቋቋም ረገድ አዲስ ነገር አሳይቶናል" ሲሉ አሞካሽተው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይህ የዶ/ር ቴድሮስ አቀራረብ ቻይና የኮሮናቫይረስን አሳሳቢነት የገለፁ ዶክተሮችን ማሠሯን ተከትሎ መሆኑ ብዙዎችን አላስደሰተም። አልፎም ቫይረሱ የዓለም ስጋት መሆኑን ለማወጅ ብዙ ጊዜ ወስደዋል ተብለውም ይወቀሳሉ።

ምንም እንኳ ዶ/ር ቴድሮስ ፖለቲከኛ ናቸው ተብለው ቢታሙም፤ ይህ እርምጃቸው ሃገራት በግልፅ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር እንዲሠሩ ያስችላል ብለው የሚያሞግሷቸውም አልጠፉም። ይህ እርምጃቸው በምዕራባውያን ሃገራት ብዙም ላይደነቅ ይችላል።

ሃላፊነት እንደተቀበሉ የያኔው የዚምባብዌ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ የጤና ሽፋንን በማስፋታቸው በሚል የዓለም ጤና ድርጅት የክብር አምባሰደር አድርገው መሾማቸው በመብት ተሟጋቾች ዘንድ ቁጣን ቀሰቀሰ። ይህን ያስተዋሉት ዶ/ር ቴድሮስ ውሳኔያቸውን ሻሩ።

አሁን ደግሞ ዓለም በኮሮናቫይረስ ስጋት ተሰቅዛ ባለችበት ወቅት ኮሮናቫረስ የዓለም ጤና ስጋት ነው ብለው ለማወጅ መዘግየታቸው ጥያቄን አጭሯል።

አንዳንዶች ኮሮናቫይረስ የከፋ ወረርሽኝ ነው [ፓንደሚክ] ብለው እንዲያውጁ ይሻሉ። ነገር ግን የድርጅቱ ነባር ሠራተኞች 'ፓንደሚክ' ማለቱ ቃል እንጂ ትርጉም የለውም ይላሉ። ድርጅቱ በሽታውን ለመግታት የሚያደርገው ጥረት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም በማለት። ድርጅቱ ከሚገባው በላይ እያካበደ ነው የሚሉም አልጠፉም።

የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ተደጋግማ የምትሰማ አባባል አለች - «ብታደርግም ትወቀሳለህ፤ ባታደርግም ትወቀሳለህ።»

ፕሮፌሰር ጎስቲን፤ ዶ/ር ቴዎድሮስ እንደውም 'የመሪነት ምሳሌ' ናቸው ይላሉ። ነገር ግን ድርጅቱ ተገቢውን በጀት እየመደበ አይደለም የሚል ስጋት አላቸው።

ነገ እንገናኝ

የዶ/ር ቴዎድሮስ እና ድርጅታቸው ስኬት ኮሮናቫይረስ በቁጥጥር ሥር እስካልዋለ ድረስ ሊታይ አይችልም።

ለአሁኑ ሃገራት እንዲዘጋጁ፣ እንዲመረምሩ እና ለመቆጣጠር እንዲሞክሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ ይመክራሉ። በየቀኑ ጋዜታዊ መግለጫ ይሰጣሉ። ለጋዜጠኞች የሚመልሱት መልስ ዋጋ አለው። እያንዳንዷ ቃል ትመነዘራለች።

ቢሆንም ሁሌ ፈገግታ አይለያቸውም። ልክ መግለጫው ሲያልቅ ፈገግ ብለው እንዲህ ይላሉ - 'ነገ እንገናኝ'