የአሜሪካ ምርጫ፡ ባይደን ወይስ ሳንደርስ? ማን ትራምፕን ይገጥማል? ወሳኙ ቀን ዛሬ ነው

Joe Biden

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩት ጆ ባይደን የትራምፕ ተቀናቃኝ መሆን የሚያስችላቸውን ነጥብ አገኙ።

በ14 የአሜሪካ ግዛቶች ዴሞክራቶችን ወክሎ ትራምፕን የሚፋለም ዕጩ ለመምረጥ በተካሄደው ቅድመ-ምርጫ ጆ ባይደን በስምንት ግዛቶች ከፍተኛ ድምፅ ማምጣት ችለዋል።

ዋነኛ ተቃናቀኛቸው በርኒ ሳንደርስ ደግሞ ብዙ ሕዝብ ያለባተት የካሊፎርኒያ ግዛትን ማሸነፍ ከቻሉ ተስፋ ቢኖራቸውም ባይደን ግን የመሪነት ደረጃውን ጨብጠዋል።

አሜሪካኖች 'ሱፐር ቲዩስደይ' እያሉ በሚጠሯት ማክሰኞ በተካሄደው በዚህ ምርጫ ሌሎች ዕጩዎችም የተሳተፉ ሲሆን ግማሽ ቢሊዮንደ ዶላር ለቅስቀሳ የመደቡት ቱጃሩ ማይክ ብሉምበርግ አንድም ግዛት ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።

የመጀመሪያዋ ሴት የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆን እየተፎካከሩ የነበሩት ኤልዛቤት ዋረን በገዛ ግዛታቸው ማሳቹሴትስ ውስጥ ሦስተኛ በመውጣት በውድድሩ ተዘርረዋል።

በዚህ ምርጫ ተፎካካሪ እጩዎቹ የሕዝብ ድምፅ ሳይሆን የተወካይ ድምፅ ለማግኘት ነው የሚፋለሙት። ሕዝቡ ድምፅ የሚሰጠው ዕጩዎቹን ወክሎ ለሚቀርብ ተወካይ ነው። በአጠቃላይ በ14ቱ ግዛቶች 1991 ተዋካዮች ሲኖሩ ከፍተኛ የተወካይ ቁጥር ያላቸው የቴክሳስና የካሊፎርኒያ ግዛቶች ናቸው።

አሁን ባለው ውጤት ጆ ባይደን 396 የተወካዮች ድምፅ ሲኖራቸው የ78 ዓመቱ አዛውንት ሳንደርስ ደግሞ 314 ድምፆች ግኝተዋል።

የኦባማ ምክትል የነበሩት ባይደን ከጥቁር አሜሪካውያን ከፍተኛ ድምፅ ማግኘታቸው ተነግሯል። አልፎም ከከተማ ወጣ ብለው የሚኖሩ ሰዎች ድምፃቸውን ለባይደን እንደሰጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በወጣቶች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው የሳንደርስ ነገርም አበቃ ማለት አይደለም። በርኒ የካሊፎርኒያ ግዛትን ምርጫ ካሸነፉ ከባይደን ጋር አንገር ለአንገት ሊተናነቁ ይችላሉ።

ሌላኛዋ ግዙፍ ግዛት ቴክሳስም የሁለቱን ሰዎች ዕጣ ፈንታ የምትወስን ናት ተብሏል። እየወጡ ያሉ ቁጥሮች እንደሚጠቁሙት ሁለቱ ተቀናቃኞች በተቀራራበ ነጥብ እየተፎካከሩ ነው።

ሁለቱም ዕጩዎች ለደጋፊዎቻቸው ንግግር አድርገዋል። 'አብዮተኛ' ናቸው የሚባልላቸው ሳንደርስ "በድሮ በሬ አርሰን ትራምፕን መርታት አንችልም። አዲስ መንገድ ያስፈልገናል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት ከምርጫ ውድድሩ ውጭ ናቸው ተብለው ጣል ጣል ተደርገው የነበሩት ጆ ባይደን ደግሞ "አልሞትንም፤ አለን" ብለዋል። የዕጩነት ፉክክሩን ጥለው ከወጡ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩዎች 'ኢንዶርስመንት' [ይሁንታ] ያገኙት ባይደን ብዙዎችን 'ሰርፕራይዝ' አድርገዋል።

ዴሞክራቶች ለሁለት የተከፈሉ ይመስላሉ። "ከባይደን እና ከሳንደርስ ማን ትራምፕን ቢገጥም አያሳፍረንም" የሚለው ሃሳብ ወጥሮ ይዟቸዋል። ሁለቱ ተቀናቃኞች ከሚያመሳስሏቸው ይልቅ የሚለያያቸው ያይላል።

ሳንደርስ 'ሶሻሊስት አብዮተኛ'፤ ጆ ባይደን ደግሞ 'ፖለቲካውን የጠጡ አርበኛ' እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።