በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሌሎች የመድሃኒቶች እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ተሰግቷል

መድሃኒቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ህንድ የምታመርታቸውን መድሃኒቶች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ወደ ውጪ መላክ ባለመቻሏ በዓለም ዙሪያ የመሰረታዊ መድሃኒቶች ዕጥረት ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

የዓለማችን ትልቋ መድሃኒት አምራች የሆነችው ህንድ ለመድሃኒቶች መስሪያ የሚውሉ 26 አይነት ግብአቶችንና ከእነሱ የሚመረቱ መድሃኒቶች ሽያጭ ላይ ክልከላ ጥላለች።

ክልከላው ከተጣለባቸው መድሃኒቶች ውስጥ በስፋት ህመምን ለማስታገስ የሚውለው ፓራሲታሞል እንደሚገኝበት ተነግሯል።

ይህ የተከሰተው ለመድሃኒቶቹ መስሪያ የሚውሉ ግብአቶችን የሚያመርቱ የቻይና ተቋማት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ምርት በማቆማቸው ወይም ምርታቸውን በመቀነሳቸው ነው።

የህንድ መድሃኒት አምራቾች 70 በመቶ የሚሆነውን የምርታቸውን ግብአት የሚያገኙት ከቻይና በመሆኑ፤ ወረርሽኙ እየተስፋፋ ከሄደ እጥረት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

"ቻይና ውስጥ የማይመረቱ መድሃኒቶች ሳይቀር ዋነኛ ግብአታቸውን የሚያገኙት ከቻይና ነው። ቻይናና ህንድ በበሽታው ከተጠቁ በዓለም ዙሪያ የመድሃኒት እጥረት ሊከሰት ይችላል" ሲሉ ሹዋን ሬን ተናግረዋል።

እጥረት ያጋጥማል ተብለው ከተሰጉት የመድሃኒቶች ዝርዝር ውስጥ ለተለያዩ ህመሞች ህክምና የሚውሉ መድሃኒቶችና ቫይታሚኖች ይገኙባቸዋል።

የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ስቴፈን ፎርማን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በመድሃኒት ግብአቶች ላይ ያጋጠመው እጥረት በዋጋ ላይ ጭማሪን እያስከተለ ነው። "ህንድ ውስጥ የመድሃኒቶች አቅርቦት መቀነስ ምልክቶች በመታየቱ በዋጋ ላይ ጭማሪ እየተስተዋለ ነው።"

ይህንን ተከትሎ የተፈጠረውን ስጋት ለማረጋጋት የህንድ መንግሥት በሰጠው መግለጫ፤ እስከ ሦስት ወር ድረስ ሊቆይ የሚችል የመድሃኒት ክምችት እንዳለው ገልጿል።

ከፍተኛ መጠን ያለው መሰረታዊ መድሃኒቶችን ከህንድ የምታስገባው አሜሪካ ህንድ በመድሃኒቶችና በመድሃኒት ማምረቻ ግብአቶች ላይ ከጣለችው ክልከላ አንጻር ሊያስከትል የሚችለውን ተጽእኖ ለመለየት እየሰሩ መሆናቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ዋና ዋና የአሜሪካ መድሃኒት አምራች ተቋማትም የምርት ግብአት የሚያገኙበትን መስመር በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑም ተገልጿል።