ኮሮናቫይረስ፡ የቫይረሱ ክትባት መቼ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል?

የኮሮናቫይረስ ክትባት ተፈብርኮ መች እንወጋው ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኮሮናቫይረስ በዓለማችን 60 አገራት ተሠራጭቷል። ገና በርካታ የኮሮና ተጠቂዎች ወደፊት ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል።

ኮሮናቫይረስን የሚገታ ክትባት እስካሁን አልተገኘም። ነገር ግን ምርመራው ቀጥሏል። አሁን ዋናውን ጥያቄ መጠየቅ እንችላለን - መቼ ይሆን የኮሮናቫይረስ ክትባት የሚገኘው?

አጥኚዎች ቫይረሱን ይገታል ያሉትን ክትባት አምርተው እንስሳት ላይ መሞከር ጀምረዋል። ይህ ማለት ሰው ላይ እስኪሞከር ወራት ሊፈጅ ይችላል። ምናልባትም በፈረንጆቹ ዓመት መገባደጃ ገደማ ሊሆን ይችላል።

ሳይንቲስቶች ክትባቱን አግኝተው ቤተ-ሙከራ ውስጥ በደስታ ፈነደቁ እንበል። ዋናው ቁም ነገር ግን ክትባቱን በገፍ ማምረት ነው።

በዚህ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ክትባቱ ተገኝቶ ጥቅም ላይ እስኪውል ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ሊፈጅ ይችላል።

አሁን ላይ ነገሮች በፍጥነት እየሄዱ ነው። ሳይንቲስቶች ክትባቱን ለማግኘት አዳዲስ መላዎች እየተጠቀሙ ነው። ነገር ግን ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ነው ማለት ከባድ ነው።

ያስታውሱ! ጉንፋን የሚያስከትሉ አራት የኮሮናቫይረስ ዓይነቶች በሰው ልጆች ሰውነት ውስጥ አሉ። ለእነዚህ የኮሮናቫይረስ ዓይነቶች እስካሁን ክትባት አልተገኘም።

ሁሉንም የዕድሜ ክልል ይታደጋል?

አዎ! ምናልባት ግን በዕድሜ የገፉ ሰዎች ተጋልጨነታቸው የከፋ ሊሆን ይችላል። ይህ የክትባቱ ባሕሪይ አይደለም። በዕድሜ የገፉ ሰዎች የመከላከል ሥርዓት አዳዲስ የመከላከያ ዘዴዎችን የመቀበል ፍጥነቱ ዝግ ያለ መሆኑ እንጂ።

ፓርሴታሞል [የህመም ማስታገሻ መድሃኒት] ቢሆን እንኳ፤ ሁሉም መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው። ነገር ግን ያለ ሙከራ ምን ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ማወቅ አይቻልም።

ክትባት ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ፍቱን መድሃኒት ነው። ነገር ግን አሁን ላይ ኮሮናቫይረስን የሚገታ ክትባት የለም። ያለው ዋነኛ መላ ንጽህናን መጠበቅ ነው።

ተላላፊ በሽታን የሚገቱ መድኃኒቶች ገበያ ላይ አሉ። ነገር ግን አንዳቸውም ሙከራ ተደርጎባቸው መከላከል ይቻሉ አይቻሉ አልተረጋገጠም።

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

የምስሉ መግለጫ,

ሩስያ ውስጥ ያለ ቤተ-ሙከራ የኮቪድ-19 ክትባትን ለማግኘት ከሚጥሩ ውስጥ አንዱ ነው

ክትባት እንዴት ይሠራል?

ክትባት ጉዳት በሌለው መልኩ ቫይረስ ወይም ባክቴሪያን ለሰውነታችን የመከላከያ ሥርዓት አጋልጦ ይሰጣል። ከዚያም የሰውነታችን የመከላከል ሥርዓት ቫይረሱን ወይም ባክቴሪያውን መከላከል ይጀምራል ማለት ነው።

ለዘመናት ክትባት ለመሥራት ጥቅም ላይ የሚውለው እራሱ ቫይረሱ ነው።

አሁን የኮሮናቫይረስን ክትባት ለማግኘት እየጣሩ ያሉ ሳይንቲስቶች አዲስ መንገድ መጠቀም ጀምረዋል። ቫይረሱን እንደ አዲስ ፈጥረው መድሃኒት ለማግኘት እየጣሩ ነው።

በሽታውን የሚያስከትለው ቫይረስ ምንም ጉዳት ከሌለው ቫይረስ ጋር ይደባልቁታል። ከዚያ የመከላከል ሥርዓታችን ቫይረሱን እንዲዋጋ ያደርጉታል።

ሌሎች ሳይንቲስቶች ደግሞ ሌላ መላ እየተጠቀሙ ነው። ወጣም ወረደ ፍቱን የሆነ ክትባት ለማግኘት ትግሉ ቀጥሏል።