አሰቃቂ መከራን አልፋ ለህይወት ስኬት የበቃቸው ሄለን

ወይዘሮ ሄለን ወረደ

የፎቶው ባለመብት, Helene Werede

ወይዘሮ ሄለን ወረደ፤ ሦስት ልጆችዋን ብቻዋ ያሳደገች ነገር ግን በድንገት ከእቅፍዋ የተነጠቀችው እናት ናት።

እስከ ዛሬዋ እለት ድረስ 'መላዕክቶቼ' ብላ የምትጠራቸውና በአሰቃቂ ሁኔታ ላጣቻቸው ለሦስት ልጆችዋ፣ ለእህቷና ለእህቷ ልጅ ያላት ፍቅር ዘላለማዊ እንሆነ ትናገራለች።

"ለብቻ ልጆች ማሳደግ ቀላል አይደለም፤ ቢከብድም ግን የልጆቼን ትምህርት በአግባቡ እከታተልና ሥራዬን እሰራ ነበር። ሦስቱም ልጆቼ የተለያየ ትምህርት ቤት ይማሩ ስለነበር እነሱን ማመላለስና መልሶ ወደ ሥራ መሄድ አስቸጋሪ ነበር" ትላለች።

ነገር ግን ግን ሁል ጊዜ በፍቅር የምትወጣው ኃላፊነት ስለነበረ እንደለመደችው እና "ስሰራበት የነበረው የሥራ መስሪያ ቤቴ ሁኔታዬን በመረዳት ያግዘኝ ስለነበር ከብዶኝ አያውቅም።"

የ13 ዓመቱ ዮሴፍ፣ የ5 ዓመቱ ያሴን ሻማምና የ6 ዓመቷ ኒስረን ሻማም፤ ሄለን በተለያዩ ጊዜያት የወለደቻቸው የህይወቷ ጌጦች ነበሩ።

ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን፤ የዚህ ቤተሰብ ህይወት ባልተጠበቀ ሁኔታ የሚቀይር ክፉ አጋጣሚ ተከሰተ።

ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በአውሮፓዊያኑ ሐምሌ 2010 ዕለተ ቅዳሜ ረፋድ ላይ፤ ሰማይና ምድር የሚያናውጥ ኡኡታ የወይዘሮ ሄለን ቤት ካለበት አካባቢ ተሰማ። ሃዘናቸውን የሚገልጹ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሲያትል ውስጥ ተሰብስበዋል።

የልጆቹ እናትም "ልጆቼን ነው የምፈልገው" እያለች ደረትዋን እየደቃች ወደ መሃል መንገድ ትሮጥ ስለነበር፤ "ሊያቅፏትና ሊያጽናኗት የሚከተሉዋት ሴቶችም ነበሩ" ሲል ሲያትል ታይምስ የወቅቱን ክስትት ጽፎ ነበር።

ሄለን በዚያች መጥፎ ዕለት በተመሳሳይ ሰዓትና በተመሳሳይ አደጋ ሦስቱንም ልጆችዋን፣ የ22 ዓመት እህቷንና የእህቷን ልጅ በድንገት አጣቻቸው።

በእያንዳንዷ ቀን ገደብ አልባ ፍቅርና እንክብካቤ በመስጠት ሳቅና ደስታ እየፈጠረች በስስት ለብቻዋን ስታሳድጋቸው የነበሩትን ልጆችዋን በእሳት አደጋ የማጣት መዓት ወደቀባት።

በወቅቱ የእሳት አደጋው በሲያትል በአስርት ዓመታት ውስጥ ያጋጠመ ከባዱ የእሳት አደጋ እንደነበርም ተነግሯል።

ሄለን ከቤተሰቦቿ ጋር በመጨረሻ ያሳለፈችውን ዕለት ፈጽማ አትረሳውም። አርብ ማታ ነበር፤ ሄለንና ሦስት ልጆችዋ፣ እህቷና የእህቷ ልጅ አንድ ላይ ፊልም በፍቅርና በደስታ ቅዳሜ መልሰው እንደሚገናኙ በማሰብ ወደ መኝታቸው አመሩ።

የፎቶው ባለመብት, Helene Werede

የምስሉ መግለጫ,

በእሳቱ አደጋ የሞቱት የሄለን ልጆች

ነገር ግን ቅዳሜ ይህ ቤተሰብ እንደወትሮው አንድ ላይ የሚያሳልፋት ቀን አልሆነችም፤ እልቁንም ሄለንን ብቻዋን ያስቀረች ዕለት ሆነች።

ከቤቱ ውስጥ የተነሳው ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ እጅግ ከባድ ነበር፤ አደጋውን ለመቆጣጠር ይጥሩ ለነበሩት የእሳት አደጋ ሠራተኞችም አዳጋች ሆነ። ከባድ ጭስና የእሳት ነበልባል ሌሊቱን በፍቅር አቅፋቸው ካደረችው ቤት መውጣቱን ቀጠለ።

እሳቱን ሊቆጣጠር የመጣው የእሳት አደጋ መኪና የውሃ ሞተር ውሃ መግፋት አልቻለም። ሌላ እርዳታ የሚሰጥ መኪና እስኪ መጣ ደግሞ ደቂቃዎች አለፉ፤ በዚህም በእሳት በሚጋየው ቤት ውስጥ ያሉትን የአምስት ሰዎችን ነፍስ ማዳን ሳይቻል ቀርቶ በእሳቱ ተበሉ።

በዚህ ክስተትም ሲያትል ላይ ከባድ ሃዘን ሆነ፤ ክስተቱን የሰሙ ሁሉ በእሳቱ ከተቀጠፉት ልጆች በተጨማሪ ከባዱ ሃዘን ለወደቀባት ሄለንም አነቡ፤ የበርካቶች ልብም በሃዘን ተሰበረ።

"ለእኔ ሁሉም ነገር ከቁጥጥሬ ውጪ ነበር፤ የውዶቼን ህይወት ማዳን የምችልበት አቅም አልነበረኝም። ስለዚህ ጉዳይ በጭራሽ ማውራት ይከብደኛል። እንዴት ብዬ ልንገርሽ? እህህህ . . . በቃ ከባድ ነው" ትላለች ሄለን ያለፈውን አስታውሶ ለማውራት አቅም እንደሌላት በመግለጽ።

ወይዘሮ ሄለን የአሜሪካ ህልም በመቋደስ የእራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ለመቀየር ላይና ታች ከሚሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዷ ነች።

"በዚች አገር ብዙ እድሎች አሉ፤ ጭንቅላታችንን ከፍተን ከፈለግን የምናጣው ነገር የለም። ዋናው ነገር ለመማርም ሆነ ለመስራት ዝግጁ መሆን ነው" ትላለች።

ሄለን ወረደ፤ እትብቷ ከተቀበረበት ቀዬ ወጥታ ወደሌላ አገር ስትሄድ ገና የሁለት ዓመት ህጻን ነበረች።

ቤተሰቦችዋ ወደ ሱዳን አቅንተው እዚያ ስምንት ዓመት ሱዳን ላይ ኖረዋል። ሄለን የ10 ዓመት ልጅ ስትሆን ደግሞ ወደ አሜሪካዋ ሲያትል ተጉዘው ኖሯቸውን እዚያው አደላደሉ።

ሄለን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ልጆች ወልዳ ልጆችዋን የማሳደግ ኃላፊነትን ለብቻዋን በመወጣት ላይ ሳለች ነበር የወጣትነት እድሜዋን ደስ እያለት መስዋዕት ያደረገችላቸው ልጆቿን በድንገት ያጣችው።

በህይወት ሁለተኛ እድል

ሄለን በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ አልፋ እናቷን፣ የሲያትል ማኅበረሰብንና ጓደኞችዋን አንስታም ሆነ አመስግና አትረካም።

ዘወትር ከልቧና ከንግግሯ የማይጠፉትን በዚያ ዘግናኝ አደጋ ያጣቻቸው ልጆችዋና እህቷ ደግሞ 'ፋይቭ ኤንጅልስ' [አምስቱ መላዕክ] ስትል ትጠራቸዋለች።

ሄለን የገጠማትን መከራ የዘወትር የሃዘኗ ምንጭ ከማድረግ ይልቅ በህይወቷ ውስጥ የሚከሰቱ መልካም ነገሮች አድርጋ ነው የምታስበው።

በሌላው አዲስ የህይወቷ ምእራፍ ያገኘቻቸውን ነገሮች በሙሉ ደግሞ፤ አምስቱ መላዕክት መርቀው ሰጥተውኛል" በማለት ፈጣሪዋን ተመሰግናለች።

"ሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። እግዚአብሔር ለእኔ ያሰበው ነገር ስለነበር ያጋጠመውን ነገር ሰጠኝ። ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼና የሲያትል ማኅበረሰብ በሰጠኝ ብርታት ሁሉንም ነገር አለፍኩት። ከዚያ በኋላም መንታ ወንድ ልጆች ተሰጠኝ። አሁን አምስት ዓመት ሆኗቸዋል። ስለዚህ ሁሉም የሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው" ትላለች።

ሄለን ከእንደዚህ አይነት እጅግ አሰቃቂ አደጋና ሞት በኋላ ለመኖር ተስፋ የምታደርግበት ሌላ ህይወት አለ ብላ ታስብ ነበር። "የነበረህን ለማጣት ምክንያት አለው። የሚያበረታህ፣ ተስፋ የሚሰጥህ ሰው አጠገብህ ሲኖር ደግሞ ሁሉንም አሸንፎ እንደገና መሳቅ፣ በህይወት መኖርና ህይወትን እንደ አዲስ መጀመር ይቻላል" ትላለች።

ከገጠማት ከባድ መከራ አንጻር "ቤት አልባ፣ የተጎሳቆለች፣ በሽተኛ ነበር የምሆነው። ግን ደግሞ እግዚአብሔር ያንን እንዳልፈው ጥንካሬ ሰጠኝ፣ ትክክለኛውን ነገር እንዳደርግ ደግሞ መራኝ። እኔም ሁሉንም ነገር ለፈጣሪዬ፣ ለእናቴና ለሁሉም ከጎኔ ለነበሩ ሰዎች አሳልፌ ሰጠኋቸው" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Helen Werede

የምስሉ መግለጫ,

በአደጋው ያጣቻቸው እህቷ፣ የእህቷ ልጅና የእሷ ልጆች

በዚህ ምክንያትም ካጋጠማት ዘግናኝ አደጋ ባሻገር ሌላ ህይወት እንዳለ ማየቷን ሄለን ትጠቅሳለች "ፈጣሪ ሌላ ህይወት ሰጠኝ፤ 'ፋይቭ ኤንጅልስ' ህይወት ሰጡኝ። እኔ ህይወትንና ያጋጠመኝ ነገር በዚህ መንገድ ነው የማያቸው" ትላለች።

ይሁን እንጂ፤ በዚህ በህይወቷ ሁለተኛ ስጦታዬ ነው በምትለው ህይወቷ ውስጥ ሁሉን ነገር "ማስረሻ" ሆነውኛል የምትላቸው "የፈጣሪ ስጦታ" ብላ የምትገልጻቸው መንትያ ልጆችዋ፤ እውነትም የእኔ ልጆች ናቸው ብላ ለመቀበል ትልቅ የሥነ ልቦና ፈተና ገጥሟት እንደበረ ትናገራለች።

"በጣም ፈታኝ የነበረው ነገር መንትያ ልጆቼን የወለድኩ ጊዜ ነው። አሁን ለእነዚህ ልጆች ሊኖረኝ የሚገባው ስሜት ምን አይነት ነው መሆን ያለበት? የሚለውን አላውቅም ነበር። ፈጣሪ ስለሰጠኝ ብቻ መውደድ ነው ያለብኝ? እውነት የእኔ ልጆች ናቸው? በሚሉ ጥያቄዎች ተወጥሬ ነበር።"

የእናት ሆድ ስለሚባባ ያለፈውን ቶሎ ለመርሳት ተቸግራ ነበር፤ ስለሆነም እቅፏ ውስጥ ያደሩትን ሦስት ልጆችዋን የነጠቃት አጋጣሚን አሁንም አሁንም ማስታወሷ አልቀረም።

በዚህ ምክንያት፤ "የወለድኳቸው ልጆች ተመልሰው ይወሰዱብኝ ይሆን? ጤነኞች ይሆናሉ? ልክ ለመጀመሪያ ልጆቼ የነበረኝ ፍቅር ለእነዚህም መስጠት አለብኝ? የሚሉ ብዙ ሞጋች ጥያቄዎች ይፈትኑኝ ነበር" ትላለች።

ነገር ግን ሄለን እንደገና ይሄንንም የህይወት ፈተና በጥንካሬ አለፈችው። ፈጣሪ የሰጣትን መንታ ስጦታ በሙሉ ልበቧ ተቀብላ እንደቀድሞዋ ዳግም ልጆችዋን በስስት የምታሳድግ እናት ሆነች።

"እነዚህ ልጆች ለእኔ ስለሚገቡኝ የእኔ ሆነዋል፤ ፈጣሪ የእኔ የሆነውን መልሶ ሰጥቶኛል፤ ብዙ ነገርም እየሰጠኝ ነው" በማለት የሁለተኛው ህይወቷን ሀሴት ትገልጻለች።

"ልጆቼን የአሸንዳ በአል እንዲያዩ ወደ ትግራይ ወስጃቼዋለው። እዛ ጥሩ ጊዜ አሳልፈን ተመልሰናል፤ ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። አሁን በየዓመቱ ልወስዳቸው ዕቅድ አለኝ። እኔ ልጅ ሆኜ ከአገር ስለወጣሁኝ እድሉን አላገኘሁም፤ እነሱ ግን በዚህ መንገድ የአገራቸውን ባህልና ሀረጋቸው ማወቅና መማር ይችላሉ።"

መልስ ወደ ትውልድ አገሯ

ሄለን ወረደ፤ እሷም ልክ ከአገሩ ወጥቶ እንዳደገ ህጻን የአፍ መፍቻ ቋንቋዋን ለመናገር በተወሰነ መልኩ ትቸገራለች።

"ሲያትል ውስጥ ትልቅ የትግራይ ተወላጆች ማህበር አለ፤ እናቴም እኔ በእንግሊዘኛ ብመልስላትም በትግርኛ ታወራኛለች። ሁል ጊዜም አገር ቤት ስላለው ወገኔ እጠይቃለው፣ ከየት እንደመጣሁ ላለመርሳት እጥር ስለነበር፣ ሰዎችም በትግርኛ እንዲያናግሩኝ እያደረግኩኝ ተምሬዋለው" ትላለች።

ሄለን ትግራይ ውስጥ ሽረ እንዳሥላሴ ከተማ ነው የተወለደችው። በሁለት ዓመቷ የተለየችውን የትውልድ አካባቢዋን ከሦስት አስርት ዓመት በኋላ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ መጥታ ያየችው። ከዚያ በኋላም አራት ጊዜ ተመላልሳ ሃገርዋን ሁኔታ ማወቅ እንደቻለች ትናገራለች።

በዚህ ዓመት ደግሞ በድንገት ባጣቻቸውና ለእነሱ ያላት ፍቅር በማይደበዝዘው በልጆቿና በእህቷ የጋራ መጠሪያ 'ፋይቭ ኤንጅልስ' ብላ የሰየመችው እና 12 ሚሊየን ብር ወጪ ያደረገችበት የሴቶችና የህጻናት የጤና ማዕከል በአገሯ ውስጥ ገንብታ አስመርቃለች።

ለምን የህጻናትና እናቶች ክሊኒክ?

ሄለን ለእናቷና ለልጆቿ ባላት ገደብ የለሽ ፍቅር የተነሳ ዋነኛ ትኩረቷ በእነሱ ላይ አድርጋለች። "የእኔ ፍላጎትም የሴቶችና የህጻናት ጤንነት ማሻሻል ነው" ትላለች።

"ልጆችን እናት ሆኖ ለብቻ ማሳደግ ምን እንደሚመስል ያየሁ ሴት ነኝ። አገር ቤት ያሉ እናቶች ህክምና የማያገኙበት አጋጣሚ እንዳለ አውቃለሁ። በዚህ ምክንያትም ለሞት ሊዳረጉ ስለሚችሉ እዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ ነው መረጥኩት" ትላለች።

በተለይ ትግራይ ውስጥ ያለውን የጤና አገልግሎት መሰረተ ልማትን ከአደግኩበት አገር ጋር ሳስተያየው እጅግ ዝቅተኛ ነው፤ "ብዙ እናቶች ይታመማሉ፣ የህክምና ድጋፍ ባለማግኘትም በወሊድ ጊዜ ልጆች ይሞታሉ። የእኔ ፍላጎትም ይሄንን ችግር መፍታት ነው።"

ወደ ኢትዮጵያ በምመጣበት ጊዜ "ብዙ አሳዛኝ ነገሮችን ስለማይ በየቀኑ አለቅስ ነበር። ልጆች የያዙ እናቶች መንገድ ላይ ማየት ደግሞ ሌላው ከባድ ነገር ነበር፤ አገር ቤት ጥሩ ነገር ሳላይ ወደ ሲያትል ተመለስኩ። እናም ለምን አንድ ነገር አላደርግም ብዬ አሰብኩ" በማለት የዕዷን መነሻ ታስታውሳለች።

ሄለን በሽረ እንዳሥላሴ ከተማ ያስገነባቸው የመጀመሪያው የጤና ማዕከል ግንባታው ተጠናቆ ባለሙያዎችና የህክምና መሳሪያዎች ተሟልተውለት አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል። ይህ የዕቅዷ የመጀመሪያ እንደሆነና ሌሎችማ ተመሳሳይ ማዕከላት በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንዲገነቡ እንደምታደርግ ትናገራለች።

በከባድ መከራ ውስጥ ያለፈችው ሄለን የገጠማትን ከባድ ፈተና በጥንካሬ ማለፍ ከመቻሏ በተጨማሪ ለወገኖቿ ለውጥና እድገት የበለጠ አስተዋጽኦ ማድረግ ትመኛለች።