ሮናሊዲኒሆ ሃሰተኛ ፓስፖርት በመያዝ ተጠርጥሮ በፓራጓይ በቁጥጥር ስር ዋለ

ሮናልዲንሆ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እውቁ የቀድሞ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሮናልዲንሆ ወደ ፓራጓይ ለመግባት ሃሰተኛ ፓስፖርት ተጠቅሟል በሚል ጥርጣሬ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተሰምቷል።

በዚህም ምክንያት የፓራጓይ ፖሊስ ሮናልዲንሆ እና ወንድሙ በፓራጓይ መዲና ያረፉበትን ሆቴል በርብሯል።

የፓራጓይ አገር ውስጥ ሚኒስትር ሮናልዲንሆና ወንድሙ እንዳልታሰሩ ነገር ግን ፖሊስ ምርመራ እያደረገባቸው እንዳለ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት ወንድማማቾቹ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ክደዋል፤ በሚደረገው ምርመራ ላይ ግን አስፈላጊውን ትብብር እያደረጉ ነው።

ሮናልዲንሆ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት በታክስ ጉዳይ እንዲሁም በሕገወጥ ግንባታ የተጣለበትን ቅጣት ባለመክፈል የብራዚልና የስፔን ፓስፖርቱን ተነጥቆ ነበር።

የፓራጓይ የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ "በእግር ኳስ ችሎታው አደንቀዋለሁ ነገር ግን ማንም ሁን ማን ሕግ ደግሞ መከበር አለበት" ሲሉ ለአዣንስ ፈራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Fiscalia Paraguay, on Facebook

የ39 ዓመቱ ሮናልዲንሆ ወደ ፓራጓይ ያቀናው አንድ መፅሃፍን ለማስተዋወቅና ስለ ችግረኛ ህፃናት ዘመቻ ለማካሄድ እንደሆነ ተገልጿል።

ሮናልዲንሆ እአአ በ2004 እና በ2005 የዓለም ምርጥ የዓመቱ እግር ኳስ ተጫዋች ሆኖ ተመርጦ ነበር።

የሮናልዲንሆ አጠቃላይ ሃብት ከ80 እስከ 100 ሚሊዮን ፓውንድ ይገመታል።