የእንግሊዝ ፍርድ ቤት ቢሊየነሩ የዱባይ ገዥ ልጆቻቸውን አግተዋል አለ

ልዕልት ሃያ ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ እንግሊዝ የተሰደዱት ባለፈው ዓመት ነበር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቢሊየነሩ የዱባይ ገዢ ሼክ ሞሃመድ ቢን ራሺድ ሁለት ሴት ልጆቻቸውን ያለፍቃዳቸው አግቶ ወደ ዱባይ እንዲመለሱ በማድረግ እንዲሁም የቀድሞ ሚስታቸውን በማስፈራራት በእንግሊዝ ፍርድ ቤት ቀርቦባቸው በነበረው ክስ ጥፋተኛ ተብለዋል።

ሼክ ሞሃመድ ላይ ክሱ የቀረበው በቀድሞ ባለቤታቸው ልዕልት ሃያ ቢንት አልሁሴን ሲሆን ብይኑ የተሰጠው ትናንት ነው።

ላለፉት ስምንት ወራት በፍርድ ቤት ሂደት ላይ የነበረውን ይህን ጉዳይ ለማጣራት ፍርድ ቤቱ እውነት አፈላላጊ ኮሚቴ አቋቁሞ ጉዳዩን ሲመረምር ቆይቷል።

ሼክ ሞሃመድ የቤተሰብና የግል ጉዳያቸው በመሆኑ የፍርድ ሂደቱ ለሕዝብ ይፋ ባልሆነ መልኩ እንዲካሄድ ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ የመጨረሻ ውሳኔውንም በይፋ አሳልፏል።

መንግሥትን የሚመሩ ሰው በመሆናቸው በእውነት ማፈላለጉ ተግባር ተሳትፎ ማድረግ ባለመቻላቸው፤ የእሳቸው በኩል ያለው ነገር ሳይሰማ ውሳኔው የአንድ ወገን እንደሆነም ተናግረዋል ሼክ ሞሃመድ።

የእንግሊዙ ፍርድ ቤት ግን በምርመራ ሂደቱ "ተባባሪም ታማኝም አልነበሩም" ብሏቸዋል።

ነገሩ የግል ጉዳይ እንደሆነ "መገናኛ ብዙሃን በእንግሊዝ የልጆቻችንን ግላዊ ህይወት እንድታከብሩና እንዳትተላለፉ እጠይቃለሁ" ሲሉ ለማስረዳት ሞክረዋል ሼክ ሞሃመድ።

ፍርድ ቤቱ ከሌላ ትዳር የተወለዱ ሁለት ሴት ልጆቻቸውን በማገትና ያለፍቃዳቸው ወደ ዱባይ እንዲመለሱ በማድረግ ሼክ ሞሃመድን ተጠያቂ አድርጓቸዋል።

ሼካ ሻምሳ በእንግሊዝ ከሚገኘው የቤተሰቡ መኖሪያ ያመለጠችው በፈረንጆቹ 2000 ነበር።

ነገር ግን ወዲያው ካምብሪጅሻየር ውስጥ በቢሊየነሩ አባቷ የደኅንነት ሰዎች ተይዛ ወደ ዱባይ እንድትመለስ ተደግጓል። እስካሁንም በዱባይ ነች።

የካምብሪጅ ፖሊስ በጉዳዩ ምርመራ ለማድረግ ወደ ዱባይ ለማቅናት ያደረገው ጥያቄም ውድቅ ተደርጓል።

ሁለተኛዋ ልጃቸው ሼካ ላቲፋ በ2002 እና በ2018 ከአባቷ ቤተሰቦች ጋር ከምትኖርበት ቤት ለማምለጥ ያደረገችው ሙከራ አልተሳካላትም። ለመጀመሪያው የማምለጥ ሙከራዋ አባቷ በሦት ዓመት እስራት ቀጥተዋታል።

ከሁለተኛው ሙከራዋ በኋላ ደግሞ የቤት ውስጥ የቁም እስረኛ እንድትሆን ተደርጓል። ለፖሊስ የላከችውን ቪዲዮ መሰረት በማድረግ ፍርድ ቤቱ ድብደባና ማሰቃየት እንደደረሰባት አረጋግጧል።

ፍርድቤ ቱም ቢሊየነሩ የዱባይ ገዢ ሼክ ሞሃመድ የሁለት ልጆቻቸውን ሰብዓዊ ነፃነት ገፍፈዋል ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የ45 ዓመቷ የዮርዳኖስ ልዕልት ሃያ የሟች ዮርዳኖስ ንጉሥ ሁሴን ልጅ ሲሆኑ የ70 ዓመቱ የዱባይ ገዢ ሼክ ሞሃመድን ያገቡት በ2004 ነበር።

የሼክ ሞሃመድ ስድስተኛ እና በእድሜ ትንሿ ሚስት ነበሩ። የሰባት እና የ11 ዓመት ሁለት ልጆችንም አፍርተዋል።

የታገቱት ሁለቱ የሼክ ሞሃመድ ትልልቅ ሴት ልጆችን በሚመለከት አባትየው መጀመሪያ ላይ ለልዕልቷ ልጆቹ ችግር ውስጥ ገብተው እንደነበር፤ በመጨረሻ ግን ከቤተሰቡ ጋር በሰላም መቀላቀላቸውን ነበር የነገሯቸው።

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ ላይ ግን ልዕልቷ ነገሮችን መጠርጠር ጀመሩ። ከዚያ ደግሞ ቅሬታቸውን መግለፅ ቀጠሉ። በሌላ በኩል ከእንግሊዛዊው ጠባቂያቸው ጋር የፍቅር ግንኙነት ጀመሩ።

ይህም ሼክ ሞሃመድን ክፉኛ አስቆጣ። ከዚያም ፍርድ ቤቱ ላይ እንደተገለፀው የሰውዬው ጠባቂዎች ልዕልቷን በተለያየ መልክ ማስፈራራት ጀመሩ። ሁለት ጊዜ የተቀባበለ ሽጉጥ ትራሳቸው ስር እንዲቀመጥ ተደርጓል።

እሳቸውን በረሃ ውስጥ የሚገኝ ሩቅ እስር ቤት ለመውሰድ ባልታሰበ መልኩ ሄሊኮፕተር ከመኖሪያቸው ቅጥር ተገኝቶም ያውቃል።

የዛሬ ዓመት የሼክ ሞሃመድ ባለቤት ልዕልት ሃያ ሁለት ህፃናት ልጆቻቸውን ይዘው ከዱባይ አምልጠው እንግሊዝ መግባታቸው ብዙዎችን ጉድ አስብሎ ነበር።

ልዕልቲቱ ለህይወታቸው መፍራታቸውን እንዲሁም ህፃናት ልጆቻቸው በአባታቸው ታግተው ወደ ዱባይ ይመለሱብኛል የሚል ስጋት እንዳለባቸው መናገራቸው ይታወሳል።

ሸሽተው ወደ እንግሊዝ ባቀኑ በአንድ ወር ውስጥ ባለቤታቸው ሼክ ሞሃመድ "አንቺም ልጆቹም መቼም እንግሊዝ ውስጥ ደህና ሆናችሁ አትኖሩም" ብለዋቸው እንደነበር ልዕልቲቱ ተናግረዋል።

ቢሊየነሩ የዱባይ ገዢ ሼክ ሞሃመድ "ኖረሻል፤ ሞተሻል" የሚል ግጥምም ማሳተማቸውን ልዕልቲቱ ይናገራሉ።