ለቀልድ ሲል አይስክሬም ከማቀዝቀዣ አውጥቶ የላሰው ወጣት እስር ተፈረደበት

ዳድሪን አንደርሰን

የፎቶው ባለመብት, JEFFERSON COUNTY SHERIFF'S OFFICE

አንድ ወጣት ቴክሳስ ውስጥ በሚገኝ መደብር ለማኅበራዊ ሚዲያ ቀልድ ሲል እራሱን በቪዲዮ እየቀረጸ ከማቀዝቀዣ አይስክሬም አውጥቶ ከላሰ በኋላ ወደ ማቀዝቀዣው በመመለሱ የ30 ቀናት እስር ተፈረደበት።

የ24 ዓመቱ ዳድሪን አንደርሰን የቀረጸው ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የታየው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ነበረ።

በዎልማርት መደብር ውስጥ ያሉ ካሜራዎች በኋላ እንዳሳዩት ወጣቱ አይስክሬሙን ከማቀዝቀዣው አውጥቶ እንደከፈለበት አሳይተዋል።

በዚህ ድርጊቱም ከእስሩ በተጨማሪ ለስድስት ወራት የሚቆይ የገደብ ቅጣት፣ የ100 ሰዓታት ያለክፍያ ሥራ፣ የአንድ ሺህ ዶላር ቅጣትና 1565 ዶላር ደግሞ ለአይስክሬም አምራቹ እንዲከፍል ተወስኖበታል።

የኤቢሲ ቴሌቪዥን እመንደዘገበው አንደርሰንና አባቱ ወደ ፖሊስ ሄደው ለላሰው አይስክሬም የከፈሉ መሆናቸውን የሚያመለክት ደረሰኝ አሳይተው ነበር።

ነገር ግን ተልሶ በተመለሰው አይስክሬም ምክንያት ለጥንቃቄ ሲል የአይስክሬም አማራቹ ድርጅት 1565 ዶላር የሚያወጡትን የቀሩትን አይስክሬሞች ለጥንቃቄ ሲል በማስወገድ በአዲስ ለመተካት ተገዶ ነበር።

አንደርሰን የፈጸመውን ጥፋት አምኖ ተቀብሏል።

ዎልማርት የተባለው መደብርም የአንደርሰን ድርጊት ይፋ ከተደረገ በኋላ ባወጣው መግለጫ "ለቀልድ በሚል በምግብ ምርቶች ላይ ተመሳሳይ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሰዎችን ከሕግ አስከባሪዎች ጋር በመሆን እንዲቀጡ እንደርጋለን፤ ይህ ቀልድ አይደለም" ሲል አስጠንቅቋል።

የአንደርሰን ድርጊት አነጋጋሪ ሆኖ ለቅጣት የተዳረገው ከወራት በኋላ አንዲት ታዳጊ ቴክሳስ ውስጥ በሚገኝ የዎልማርት መደብር ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ አይስክሬም ከማቀዝቀዣ አውጥታ ልሳ ስትመልስ የሚያሳይ ቪዲዮ ከታየ በኋላ ነው።

ከ18 ዓመት በታች የሆነችው ታዳጊ አይስክሬሙን ያልገዛችው ሲሆን ቪዲዮው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከ13 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ታይቷል። የአንደርሰንንም ጉዳይ ቀስቅሶ ለቅጣት ዳርጎታል።