ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ ግብጽን በመደገፍ ያወጣውን የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ አደረገች

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አርማ

የፎቶው ባለመብት, MOFA

የአረብ ሊግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትላንት ካይሮ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ግብጽን በመደገፍ ያወጣውን የውሳኔ ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ እንደማይቀበለው የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ሊጉ በግድቡ ዙሪያ እየተደረገ ያለውን ድርድር ቁልፍ እውነታዎችን ሳያገናዝብ በውሳኔ ሃሳቡ የሰጠው ጭፍን ድጋፍ እንዳሳዘነው አመልክቷል።

መግለጫው በተጨማሪም የውሳኔ ሃሳቡን እንደማትቀበል አሳውቃለች የተባለችውን የሱዳንን አቋም ያደነቀ ሲሆን፤ ከግድቡ አንጻር በተቀነባበረው የአረብ ሊግ አቋም ላይ "ሱዳን በድጋሚ ለምክንያታዊነትና ለፍትህ ያላትን አቋም አሳይታለች" ሲል አወድሷታል።

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ እንዳለው ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ይዛው የቆየችውን "የአሁኑንና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት የአባይ ውሃ ሃብቷን የመጠቀም መብቷን" ታስከብራለች። አባይ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ እንደመሆኑ ውሃውን ከሚጋሩ አገራት ጋር በመተባበር መርህ ጉልህ የሆነ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ ፍትሃዊና ተቀባይነት ባለው መንገድ መጠቀምን ትደግፋለች።

በተጨማሪም በግልጽ በሚደረግ ውይይት ሁሉንም የሚጠቅም ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል ኢትዮጵያ እንደምታምን መግለጫው አመልክቷል። የበላይነት ለመያዝ የሚደረግ ጥረት ውጤት የማያመጣ ከመሆኑ በተጨማሪ አሁን ባለው አገራት እርስ በርስ ተሳስረው በሚኖሩበት ዘመን ቦታ የለውም ሲል የጋራ ተጠቃሚነትን አስፈላጊነት ጠቅሷል።

ግድቡን በውሃ ለመሙላትና የውሃ አለቃቀቅን በተመለከተ መሰረት ለሆነውና ቀደም ሲል ለተደረሰው የመርህ ድንጋጌ ስምምነት ኢትዮጵያ ተገዢ መሆኗን እንደምታረጋግጥና በዚህ ስምምነትም የመጀመሪያ ደረጃ የግድቡ የውሃ ሙሌት ከግድቡ የግንባታ ሂደት ጋር ጎን ለጎን ይካሄዳል እንደሚልም መግለጫው አመልክቷል።

በመጨረሻም መግለጫው የአረብ ሊግ ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ዘመናት በነበረው ግንኙነትና የጋራ ዕሴቶች አንጻር ከእውነት ጋር እንደሚቆም እምነት እንዳለው ጠቅሶ ወደፊትም ለጋራ ግብ በቅርበት ለመስራት እንደሚፈልግ ገልጿል።

በተያያዘ ዜና ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንጻር አገራዊ ክብርን አሳልፎ የሚስጥ ስምምነት ውስጥ መንግሥታቸው እንደማይገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ትናንት መናገራቸው ተዘግቦ ነበር።

የብልፅግና ፓርቲ የአመራሮች ሥልጠና ማጠቃለያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት "ከውጭ ለምናገኘው ሀብት ብለን አገራዊ ክብራችንን አሳልፈን አንሰጥም" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም በመልዕክታቸው ግድቡ የሌሎችንም ሀገራት ጥቅምን በማይጋፋ መልኩ አጠናቀን ጥቅም ላይ እናውለዋልን ሲሉም አምልክተዋል።

ጨምረውም "ምንም እንኳ ቀደም ብለን ማጠናቀቅ ቢኖርብንም፤ በባለፈው ሳንቆጭ የያዝነውን ሳንለቅ ግድቡን አጠናቀን የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ባለፈው ቅዳሜ ያወጡት መግለጫ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናትና ከህዝቡ ጠንካራ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን በሂደቱ የአሜሪካ ገለልተኝነት ላይ ከተለያዩ ወገኖች ጥያቄን አስነስቷ።

የአሜሪካ መግለጫ የድርድር ሰነዱ ሳይፈረም በዚህ ዓመት መገባደጃ ላይ ይጀመራል ይተባለው የውሃ ሙሌት ሥራ መካሄድ እንደሌለበት በአጽንኦት ቢያስቀምጥም ኢትዮጵያ በዚህ እንደማትስማማ አሳውቃለች።