አሚን ዳንኤል፣ ቀና ዘመድኩንና ዳንኤል ለማ፡ ማወቅ የሚገባችሁ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ሙዚቀኞች

አሚን ዳንኤል፣ቀና ዘመድኩን፣ዳንኤል ለማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተወለዱበትን ቀዬ ለቆ፣ ባህልና አኗኗር ዘዬ፣ ዘመድና ቤተሰብ ትቶ መሰደድ ምን አይነት ስሜት ይኖረው ይሆን?

አገራቸው በጦርነት ፈራርሶ፣ ቤታቸው በጦርነት ወድሞ፣ በፖለቲካ እምነታቸው ተሳዳጅ ሆነው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ነገን በማለም የነጎዱትን ታሪክ ይቁጠረው።

ኢትዮጵያውያን ወደ ሌላ አገራት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ያጠኑ ሰዎች እንደሚሉት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህዝብ ስደት የተጀመረው በደርግ ወቅት ነው።

የተለያዩ አፍሪካ አገራት በተለይም ሱዳን የብዙዎች መቀመጫ ነበረች፤ ከዚያም ነገን ተስፋ ወደ ፈነጠቁላቸውም ምዕራቡ ዓለም።

ምንም እንኳን ካደጉበት አገር፣ ባህል መነቀል ቀላል ባይሆንም በህይወት የተረፉ ስደተኞች ከዜሮ ጀምረው ኑሮን መስርተዋል፤ ልጆቻቸውን አሳድገዋል፣ ለቁም ነገር አብቅተዋል።

ይህ ሁኔታ የጃማይካዊቷ ፀሀፊ ኤድዊጅ ዳንቲካትን "ሁሉም ስደተኞች አርቲስቶች ናቸው" የሚለውን አባባል ያስታውሳል። ፀሃፊዋ ይህንን የምትልበት ምክንያት አላት ይህም ስደተኞች ከስር መሰረታቸው ተነቅለው፣ ከዜሮ ጀምረው፣ አዲስ ህይወት መስርተው ቤትን አገርን በሚመስላቸው መልኩ ስለሚቀርፁት ነው።

ይሄ የኢትዮጵያውን ስደተኞች ብቻ እውነታ ሳይሆን የብዙ አገራት ስደተኞች ነው። የእነዚህ ስደተኞች ልጆችስ ኑሮ ምን ይመስላል፤ እስቲ በሌላው አለም እያንፀባረቁ ያሉ መኖሪያቸውን በምዕራቡ አለም ያደረጉ ሙዚቀኞችን ታሪክ በትንሹ እናጋራችሁ።

የፎቶው ባለመብት, Scott Dudelson

የምስሉ መግለጫ,

አሚኔ ዳንኤል

አሚ ዳንኤል- እምቢተኛው

በዓለማችን ውስጥ በቀለም፣ በማንነት በዘር እንዲሁም በተለያዩ እምነቶች ጭቆና እንደሚደርስበት ለማወቅ ምናልባት በሚጨቆኑ ሰዎች መንገድ ማለፍ ይጠበቅ ይሆን? ከታሪክ፣ ከመፃህፍትና ከተጨቆነ የማኅበረሰብ ክፍል አንደበት መረዳት አይቻል ይሆን? ለብዙዎች እልቂት ከሆነው ጦርነቶች፣ ህመሙ ለትውልድ ትውልድ ከተረፈው የባርነት ታሪክ፣ ጠባሳው ካልሻረው ቅኝ ግዛት ምን ያህል ተምረን ይሆን?

የዓለማችንን ነባራዊ ሁኔታ ስናይ ሌላ አይነት ጭቆና እልቂት እንደቀጠለ ነው። ለዛም ነው ብዙዎች በጥበባቸው፣ በፅሁፎቻቸው፣ በሰልፎች እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለማሰማት የመረጡት።

ኢትዮጵያዊው አሜሪካዊ ራፐር አሚኔ ዳንኤል ቀልድ በተዋዛበት መልኩ ያወጣው 'ሬድ መርሰዲስ' ጥቁሮች የሚደርስባቸውን መገለልና ዘረኝነት በቀልድ መልኩ ጠቆም ያደርጋል።

እስቲ የኃይል አሰላለፉ ተገለባብጦ ነጮች አሁን ያሉበትን የጥቁሮች ቦታ ሲይዙና አድልዎና ዘረኝነቱን በመገልበጥ ያሳያል። በቪዲዮውም ላይ ነጭ የቆዳ ቀለም አድርጎ መታየቱም አወዛጋቢም አድርጎት ነበር፤ የተናደዱበትም ነበሩ መልእከቱንም የተረዱ እንዲሁ።

'ሬድ መርሰዲስ'ም በቢልቦርድ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ በመቶዎች ዝርዝር አስራ አንደኛ ሆኖ ለ28 ሳምንታት ያህል የቆየ ሲሆን፤ 221 ሚሊዮን ተመልካቾችም ቪዲዮውን አይተውታል።

በራፕ ሙዚቃ መድረክ ውስጥ ስም እያተረፈ ያለው አሚኔ የሚያምንበትን ነገር ከመዝፈንም ሆነ ከመናገር ወደ ኋላ አይልም። በቅርቡ ጂሚ ፋለን የሚያቀርበው ታዋቂው ፕሮግራም "ዘ ቱ ናይት ሾው" ላይ ትራምፕን ወርፏቸዋል።

"አሜሪካን ታላቅ አታደርጋትም፤ ያደረከው በሙሉ ጥላቻን ማስፈን ነው፤ ትራምፕ የሚሰራውን የማያውቅ ግለሰብ ነው፤ ምንድን ነው የሚለው? ይህቺ አገር እኮ የስደተኞች ናት" ብሏል።

ለአሚኔ ስደተኝነት በቅርቡ የሚያውቀው ነው፤ ብዙ ሳይርቅ የቤተሰቦቹ ታሪክ ነው፤ እናቱ እፀ ህይወትና ዳንኤል ከኢትዮጵያ ተሰደው ነው ፖርትላንድ የከተሙት፣ ኑሮን በባዕድ አገር 'ሀ' ብለው የጀመሩት፤ ቤትን የመሰረቱት።

እናቱ የሚሰሩት ፖስታ ቤት ሲሆን አባቱ ደግሞ መምህርና አስተርጓሚ ናቸው። አሚኔ ነጭ ተማሪዎች በብዛት ባሉበት ትምህርት ቤት ነው የተማረው፤ ገና በልጅነቱ ጥቁር መሆኑን የሚያስታውሱት ጨቅላ ህፃናት ከቤተሰባቸው የወረሱትን ጥላቻን በማንፀባረቅ 'ኒገር፣ ኒገር' ሲሉት ነው ያደገው።

"ሁሌም ቢሆን የባዳነት ስሜት እንደተሰማኝ ነው፤ ያ ወቅት ለእኔ አሰቃቂ ነበር" ይላል።

ከትምህርት ቤት ሲወጣ ግን ጥላቻውንም ሁሉንም ይረሳዋል፤ ቤት ውስጥ ቤተሰቦቹ አማርኛ ያወራሉ። የኢትዮጵያ ሙዚቃም ያደምጣሉ።

ከኢትዮጵያ ሙዚቃ በተጨማሪ እናቱ ደግሞ ቱፓክ ሻኩርን፣ ማይክል ጃክሰን፣ ጆን ሜየርና ካንዬ ዌስትን የመሳሰሉ ሙዚቃ አስተዋወቀችው። ሙዚቃው እንዲሁም የቤተሰቡ ታሪክ ውስጥ ራሱን ይከታል፤ የትምህርት ቤት ዓለምንም ይረሳዋል።

አንደኛ ደረጃ በገጠመው ከፍተኛ ጥላቻ በብዙ መልክ የተቀየረው ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሌላ ትምህርት ቤት በመቀየሩ ነው፤ ጓደኞችም አፈራ። በትምህርቱም ጎበዝ ነበር። ወደ ሙዚቃው ዓለምም የገባው በዚህ ወቅት ነው።

የፎቶው ባለመብት, Scott Dudelson

የምስሉ መግለጫ,

አሚኔ ዳንኤል

በሙዚቃው ቀጠለበት ፖርትላንድ ስቴት ዩኒቨርስቲ ማርኬቲንግ እያጠናም ሙዚቃውን ተደብቆ ይሰራ ነበር። ነገር ግን ቀላል አልሆነለትም፤ ሙዚቀኞችም ሆነ አቀናባሪዎች ከእሱ ጋር ተጣምረው መስራት አልፈለጉም፤ ለስቱዲዮ ከፍሎ መስራት ደግሞ በተማሪ አቅም ገንዘብ ከየት ይምጣ፤ የማይታሰብም ሆነ።

ለዚያም ነው አሜሪካ ውስጥ ዘረኝነት ቢኖርም "የደቡቡ ክፍል ዘረኝነት ይለያል" የሚለው። ጥቁር በመሆን ብቻ ሥራ፣ መኖሪያ ቤት አለማግኘት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች የብዙዎችን ጥቁሮች ህይወት ያከበዱ ናቸው።

ነገር ግን ለራሱ መላ በመዘየድ ከአምስት ዓመታት በፊት ራሱ ላፕቶፑ ላይ የቀዳውና ያቀናበረው 'ካሮላይን' የተሰኘ ሙዚቃው ብዙዎችን ያስደነቀ ነጠላ ዘፈን ሆነ። በዚህ ሙዚቃውም ከሚታገል ኮሌጅ ተማሪ የሂፕ ሆፕ ኮከብም ሆነ። ቪዲዮውንም 175 ሚሊዮን ተመልካች አየው። ከዚህም በተጨማሪ ካሮሊን ሶስት ጊዜ የፕላቲኒየም ደረጃ ላይ ደርሷል።

የመጀመሪያው አልበሙ "ጉድ ፎር ዩ" ከሦስት ዓመት በፊት የወጣ ሲሆን ራፕ፣ ኢንዲ ሮክንና ሌሎችንም ስልቶች አጣምሮ ይዟል፤ በዚህም አልበም ከፍተኛ ተቀባይነትን ማግኘት ችሏል።

ኒውዮርክ ታይምስ "የራሱን ስልት የፈጠረ" በማለት ያንቆለጳጰሰው አሚኔ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት የራሳቸውን ድምፅ መፍጠር የቻሉትን ካንዬ ዌስት፣ አንድሬ 3000፣ ፋረል ዊልያምስን በአንድ ላይ ማምጣት የቻለ ነው ብሎታል።

ከኤርትራዊና ኢትዮጵያዊ ስደተኞች የተወለደው የ25 ዓመቱ ራፐር ቅርጫት ኳስ የመጫወት ህልም ነበረው፤ ህይወት የራሷ ሌላ እቅድ ስላላት ወደ ሙዚቃው ዓለም ወሰደችው።

የፎቶው ባለመብት, Gregg DeGuire

የምስሉ መግለጫ,

ቀና ዘመድኩን

ቀና ዘመድኩን - የማህበራዊ ፍትህ ታጋዩ

በኢትዮጵያ አንድ አባባል አለ፤ "ስምን መልአክ ያወጣዋል" የሚል፤ አባባሉ ሰምና ወርቅ አለው። ሰሙ ስም ዝም ብሎ በዘፈቀደ አይወጣም የሚል ሲሆን ወርቁ ግን የአንድ ሰው ተግባሩ ከስሙ ጋር በጥሩም ይሁን በመጥፎ ሲገናኝ ሁሉን የሚያውቁ አወጡት ለማለት ነው።

ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊው ቀና ዘመድኩንም ይሄንን አባባል የወረሰ ይመስላል። ስሙን የሰጠው አባቱ ሲሆን ስሙም በህይወቱ ትልቅ ትርጉም አለው፤ ለቀናነትም ትልቅ ቦታ ይሰጣል። ቤተሰቦቹ እንዳወረሱት ስምም መኖር ይፈልጋል። ብዙዎች በዚያው መንገድ እየኖረ መሆኑንንም ተግባሩን በማየት ይመሰክሩለታል።

የ41 ዓመቱ ቀና ዘመድኩን ሙዚቀኛ፣ ፀሃፊ፣ የቴክኖሎጂ ፈጣሪ እንዲሁም የማህበራዊ ፍትህ ታጋይም ነው። ሙዚቃው ለግራሚ፣ ኤሚ እንዲሁም ቪኤምኤ ታጭቷል። ቀና ከሙዚቀኝነቱ በተጨማሪ በዓለም አቀፉ ውስጥ ያለውን የውሃ እጥረት፣ አቅርቦት ችግርም ለመፍታት በብዙ ሚሊዮኖች ዶላርም ለማሰባሰብ ችሏል።

"ገንዘብና እውቅና ሳይሆን ሥራዎቼ ለሌሎች ህይወት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ እፈልጋለሁ፤ እንደ አርቲስትም የመረጥኩትም መንገድ እሱን ነው" ብሏል በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ መጠይቅ።

ለምሳሌ "ሌትስ ስታርት ኤ ሪቮሉሽን' የሚለውን ሙዚቃውን ብንወስድ በአጠቃላይ ነገሮችን ከስር መሰረት መቀየር የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ ይዟል። ቀና ሙዚቃዬ ምን ያህል ተፅእኖ አለው? የተሻለ ሰው መሆንን አነሳስቷችኋል? በጎ ነገር እንድታደርጉ ገፋፍቷችኋል? ከዚህ በፊት ስለ ራሳችሁ የማታውቁትን ነገር እንድታውቁ አድርጓችኋል ወይ ብሎ ይጠይቃል።

የተለያዩ የሙዚቃ ስልቶችን በማጣመር የሚመራመረው ዳንኤል ኤሌክትሮኒካ፣ ሲንተቲክ ፖፕ፣ ፖስት ሮክ እንዲሁም ሃውስ የሚጫወተው ቀና 'ሰይ ጉድባይ ቱ ላቭ' የሚለውም ሙዚቃው ምርጥ የከተማ (ኧርባን) አማራጭ በሚልም ለ2009 ግራሚ ታጭቷል።

ሙዚቃዎቹ ሲወጡ የአሜሪካ የሙዚቃ ሰንጠረዥን የሚቆጣጠሩ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 'ፍሪ ታይም' አልበሙን መጥቀስ ይቻላል። አንደኛው አልበሙም 'ሂት ሲከርስ' በሚባለው የአሜሪካ የሙዚቃ ሰንጠረዥ አንደኛ ሆኖ ነበር።

በሙዚቃው ውስጥ ሳም ኩክ፣ ናት ኪንግስ፣ ፍራንክ ሴናትራ ከፍተኛ ስፍራ ያላቸው ሲሆን ልክ እንደነሱም መንፈስን ሰርስሮ የሚሰርፅ፣ ወደሌላ ዓለም የሚያመጥቅ ሙዚቃን መስራት ይፈልጋል።

ቀና የተወለደው ኢትዮጵያ ሲሆን እስከ ሦስት ዓመቱም ያደገው በአያቱ ቤት ነው። ወላጅ አባትና እናቱ የደርግን መንግሥት ሸሽተው ወደ እንግሊዝ ከዚያም ወደ አሜሪካ አቀኑ፤ ቀናም ወላጆቹን የተቀላቀለው በዚህ ወቅት ነበር።

ገና በታዳጊነቱ ወደ ሙዚቃው ዓለም የመጣው ቀና፤ ራሱን ፒያኖ በማስተማርም ስቲቪ ወንደር፣ ማርቪን ጌይ እንዲሁም ዘ ኪውርና ዱራን ዱራን ቡድኖችን ሙዚቃ አጥንቷል።

ቀና በተለያዩ አልበሞቹ ከፋረል ዊልያምስ እንዲሁም ከራፐሩ ቸንጅ ጋር በመጣመር ሙዚቃዎችን የሰራ ሲሆን፤ ከሙዚቃው በተጨማሪ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገራትን የውሃ ችግር ለመፍታት በሚል ከሙዚቀኛ ጓደኛው ሉፔ ፊያስኮ እንዲሁም ከሌሎች ታዋቂ ሰዎች ጋር በመሆን የኪሊማንጀሮ ተራራን በ2010 ወጥተዋል። 'ተርን' የሚለውም የዘፈኑም ሽያጭ ለዚህ ፕሮጀክት ውሏል።

የምስሉ መግለጫ,

ዳንኤል ለማ

ዳንኤል ለማ- ለአገሩ ባዳ

ከኢትዮጵያ በሺዎች ኪሎ ሜትር ርቆ በአውሮፓዊቷ አገር በስዊድን ታዋቂ የሆነውን ዳንኤል ለማን ያውቁት ይሆን?

ምናልባት ኑሯችሁ በስካንድኔቪያን አገራት በአንዱ ከሆነ በተለያዩ ፌስቲቫሎች ላይ ጊታሩን ይዞ ለስለስ ያለ ሙዚቃውን ሲጫወት አይታችሁት ይሆናል። እነ 'ማይ ቨርዥን'፣ 'ሪባውንድ'፣ 'ድሪመርስና ፉልስ'፣ 'ሳም በዲ ኦን ዩር ሳይድ' የመሳሰሉ ዘፈኖቹን ካወቃችሁት ደግሞ አብሮ አለመዝፈን ከባድ ነው።

ፌስቲቫሉ ቀርቶ ድንገት ሥራ ላይ ሆናችሁ 'ኢፍ አይ ዩዝድ ቱ ላቭ ዩ'ን እየሰማችሁ 'ላይክ ኤ ሬይንቦው ራይት ናው' የሚለውን ሃረግ አለመደጋገም አይቻልም።

የ48 ዓመቱ ዳንኤል የተወለደው ኢትዮጵያ ነው። ወደ ስዊድን ደግሞ ያቀናው ገና ነፍስም ሳያውቅ በጨቅላነቱ ቤተሰቦቹ የተሻለ ህይወት ይኖራል በሚል በጉዲፈቻ ሰጥተውት ነው።

ለዳንኤል ሙዚቃው ያለፈበት ጉዞን፣ ህልሙ ተስፋውና ፀፀቱ፣ የተደራረቡ ማንነቶች መግለጫው ነው። ሙዚቃው ከብዙ ነገር ማምለጫም ሆነ መግለጫም ሆኖታል።

ምናልባት የአውሮፓ ኑሮ ምቹ ከመሆኑ አንፃር ስዊድን ማደግ ቀላል ሊመስል ይችላል፤ ለዳንኤል ግን ከባድ ነበር። ምክንያቱም ብቸኛው ጥቁር ልጅ በክፍሉ ውስጥ እሱ ስለነበር።

የዳንኤል ሙዚቃ ጉዞ የሚጀምረው ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ነው፤ ባንድም መሰረቱ ። ከመዝፈን በተጨማሪም ከበሮም ይጫወት ነበር። ባንዱም እያደገ መጣ፣ ዳንኤልም ሙዚቃ ወደ መፃፉ ጠልቆ ገባ።

በመጀመሪያ አካባቢ ቀላል አልነበረም፤ መድረክ ላይ ብዙ ሰዎች ፊት መዝፈን፤ የመድረክ ፍራቻውም እንዲሁ እስኪለምደው ድረስ።

መጀመሪያ አካባቢ የራሱ ባይሆንም የታዋቂው አሜሪካዊ ሙዚቃ ቦብ ዲለንን ይጫወት ነበር እንዲሁም የምንጊዜም ጀግናዬ የሚለውን የሬጌውን ንጉሥ ቦብ ማርሌንም ይጫወት ነበር፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የኖረውም አልበም የቦብ ማርሌይ ነው።

በተለይም በነጭ አገር ውስጥ እሱን የሚመስል ሰው በሚዲያው ላይም ሆነ በአካባቢው አለመኖር የቦብ ማርሌ ሙዚቃ ሊኖርበት የሚችል ሌላ ዓለም ፈጠረለት። ቦብ ማርሌን ሙዚቃውን ብቻ ሳይሆን ለዳንኤል ፀጉሩን ድሬድ ለማድረግ መነሻ ሆነው።

ከቦብ ማርሌ በተጨማሪ የታዋቂዋን ጥቁር አሜሪካዊ ፀሐፊና የከለር ፐርፕል ደራሲ አሊስ ዋከርን 'ኦፕረስድ ሄይር' (የተጨቆነው ፀጉር)ን ማንበቡ ነፃነት ከፀጉር እንደሚጀምር ለመረዳት እንዳስቻለው በአንድ ወቅት ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Daniel Lema Album cover

የምስሉ መግለጫ,

ዳንኤል ለማ

ሙዚቃውንም በጎን እየተጫወተ ሥነ መለኮትና ታሪክን በደቡብ ስዊድን ከሚገኘው ሉንድ ዩኒቨርስቲ አጥንቷል።

ከዚያም ኑሮውን ለሦስት ዓመታት ያህል በኒውዮርክ ያደረገው ዳንኤል የመጀመሪያ አልበሙን ቢያጠናቅቅም በአንዳንድ እክሎች ምክንያት ሳይለቀቅ ቀረ።

ቢሆንም የኒውዮርክ የተለያዩ የሙዚቃ መድረኮችን እንዲያይ እድሉን ሰጥቶታል፤ በተለያዩ ክለቦችም ተጫውቷል።

ወደ ስዊድንም ተመልሶ በዓመታት ውስጥ ስድስት አልበሞችን ሰርቷል፤ በተለይም 'ያላ ያላ' ለሚለው ፊልም የሰራው ማጀቢያ 'ኢፍ አይ ዩዝድ ቱ ላቭ ዩ' ለግራሚ እንዲታጭ አድርጎታል። ፊልሙ በስዊድን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በስካንድኔቪያን አገሮች ታዋቂነትን አትርፏል።

ምንም እንኳን ስዊድን ውስጥ በራሳቸው ቋንቋ የሆኑ ሙዚቃዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተደማጭነት ቢኖራቸውም፤ ዳንኤል በእንግሊዝኛ በሚዘፍናቸው ሙዚቃዎቹ በሙዚቃው መድረክ ላይ ጎልቶ ለመታየት ችሏል። ሆኖም ግን ጥቁር መሆኑ ያለውን ተፅእኖ አይደብቅም።

የምስሉ መግለጫ,

ዳንኤል ለማ

ከሬጌም በተጨማሪ ብሉዝ፣ ሶውል፣ ጎስፔል፣ ሮክ፣ ሐገረሰብ ሪትም ኤንድ ብሉዝን በመቀላቀል ይጫወታል።

"ሙዚቃዎቼ ለሰዎች በህይወታቸው ትርጉም እንዲሰጣቸው እፈልጋለሁ። ጠዋት ለምን ይነሳሉ? የሚሰሯቸውንስ ሥራዎችስ ለምን ይሰራሉ? የህይወትስ ትርጉሙስ ምንድን ነው የሚለውን በሙዚቃዎቼ በተወሰነ መልኩ መመለስ እፈልጋለሁ" ይላል።

የማደጎ ቤተሰቦቹ ማንነቱንም ሆነ ስለቤተሰቦቹ እየነገሩ ነው ያሳደጉት በዚያም ምክንያት ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ከአዕምሮው እንደማትጠፋ ይናገራል።

በሃያዎቹ ዕድሜ መጨረሻም ቤተሰቦቹ ጋር ሊገናኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ቤተሰቦቹ ጋር መገናኘት ቀላል አልነበረም ነጭ አገር ለምን ሰደዱኝ የሚሉ ያልተመለሱ ጥያቄዎች፣ የማንነትን መቀማት ፀፀት እንዲሁም ወላጆቹን መቀበልም አዳግቶት እንደነበር በአንድ ወቅት ተናግሯል። ቢሆንም ቤተሰቦቹንም ሆነ ተቀማሁ የሚለውን ማንነት ለማጥናት ቁርጠኛ ነበረ።

ከቤተሰቦቹ ጋር ከመገናኘት በተጨማሪ ስለ አገሩ ሙዚቃ አንደ አዲስም መማር ጀመረ። ከዚያ በኋላ መመላለስ የጀመረው ዳንኤል በተለያዩ መድረኮች በዓመታዊ የሰላም ፌስቲቫል በግዮን እንዲሁም በኮፊ ሃውስ ለኢትዮጵያውያን አድማጮች የመጫወት እድሉን አግኝቷል።