ክሊንተን ከሞኒካ ሊዊንስኪ ጋር ግንኙነት የጀመርኩት ከጭንቀት ለመውጣት ስል ነበር አሉ

ቢል ክሊንተን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንትን ረዳታቸው ከነበረችው ሞኒካ ሊዊንስኪ ጋር የፍቅር ግንኙነት የጀመሩት በወቅቱ ከነበሩበት የጭንቀት ስሜት ለመውጣት ሲሉ እንደነበር ተናገሩ።

ክሊንተን ይህን አወዛጋቢ ነገር የተናገሩት እንደ አውሮፓውያኑ 2016 እጩ ፕሬዝዳንት በነበሩት ባለቤታቸው ሂላሪ ክሊንተን ፖለቲካ ህይወት ዙሪያ በሚያጠነጥነው 'ሂላሪ' በተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ላይ ነው።

በ1998 ከሞኒካ ሊዊንስኪ ጋር በነበራቸው የፍቅር ግንኙነት ዙሪያ በሚደረግ ምርመራ ላይ በመዋሸታቸው ተከሰው የነበሩት ቢል ክሊንተን በመጨረሻ ከሴኔቱ ፊት ቀርበው በነፃ ተሰናብተዋል።

ክሊንተን በትዳራቸው ላይ በመወስለት ከሊዊንስኪ ጋር ፍቅር ሲጀምሩ ሊዊንስኪ በዋይት ሃውስ የተቀጠረች የ22 ዓመት ተለማማጅ ሠራተኛ ነበረች።

የክሊንተንና የሞኒካ ሊዊንስኪ ግንኙነት በ1990ዎቹ የመገናኛ ብዙሃን ዋነኛ ዜና ነበር። መጀመሪያ ላይ የፕሬዘዳንቱ ነገሩን መካዳቸውና በመጨረሻም "ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት ነበረን" ሲሉ ማመናቸው ነገሩን አጡዞት ነበር።

መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን መጀመሪያ ላይ አደባባይ ሲያወጡት "ከዚያች ሴት ጋር ፆታዊ ግንኙነት አልነበረኝም" የሚለው የክሊንተን ንግግር በስላቅ መልክም ቢሆን እስከዛሬም በአሜሪካ ፖለቲካ የሚታወስ አባባል ሆኖ ቀርቷል።

በጊዜው ሊዊንስኪ በበኩሏ ከፕሬዘዳንቱ ጋር የነበራት ግንኙነት በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንደነበር ብትናገርም "ነገሩ ግን ስልጣንን ያላግባብ መጠቀም ነው" ብላ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በጊዜው ከፕሬዘዳንቱ ጋር የጀመረችው ግንኙነት ምን መዘዝ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል የነበራት መረዳት ውስን እንደነበር፤ አልፎ ነገሩን ስታስበው እንደምትፀፀት ተናግራ ነበረች።

በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ክሊንተን የሊዊንስኪ ህይወት በተፈጠረው ነገር ብቻ መተርጎሙ እጅግ እንደሚያሳዝናቸው ይናገራሉ።

ሂላሪ ክሊንተን በጊዜው ስለተሰማቸው ነገር ሲጠየቁ በሚያሳየው የዘጋቢው ፊልም ክፍል ላይ "ማመን በማልችለው ደረጃ በጣም ተጎድቼ ነበር። መዋሸትህን ማመን አልችልም እናም ይህ ነገር አደባባይ የሚወጣ ከሆነ ለቼልሲ [ልጃቸው] የምትነገራት አንተ ነህ" ይላሉ።

ወዲያው ከባለቤታቸው ክሊንተን ጋር ምንም ዓይነት ነገር እንዲኖራቸው አልፈለጉም ነበር። በመጨረሻ ግን በትዳር አብረው ለመቀጠል ወሰኑ ሂላሪ ክሊንተን።

"አንዳንድ ሰዎች ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነ አሰቡ፤ አንዳንዶች ደግሞ ስህተት ነው አሉ" ሲሉ ያስታውሳሉ ሂላሪ።

እውነቱን ለልጃቸው ቼልሲ መንገር እጅግ ከባድ እንደነበር ቢል ክሊንተንም ያስታውሳሉ - በዘጋቢ ፊልሙ ላይ።