ለአባልነት ዲግሪ ሲጠይቅ የነበረው ፓርቲ ለምርጫው ምን እያደረገ ነው?

አንዱአለም በእውቀቱ

የፎቶው ባለመብት, Andulalem bewketu

የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ ዛሬ ላይ ባለው ቅርፅ ከመጣ የተቆጠሩት ገና ጥቂት ወራት ብቻ ቢሆኑም የፓርቲው አመራር ውስጥ በ1997ቱ ምርጫ ጎልተው የታዩ ፖለቲከኞች እንዲሁም ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (ኢብን) ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ወጣቶችም አሉበት።

ከቀናት በፊት ፓርቲው በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ፊርማ "ያሰባሰብኩበት ሰነድ በፀጥታ ኃይሎች ተነጠቀብኝ" በማለቱና በሌሎች ፓርቲውን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ የፓርቲውን ምክትል ሰብሳቢ አቶ አንዱአለም በእውቀቱ ገዳን አነጋገረናል።

ፊርማ ያሰባሰባችሁበት ሰነድ እንዴት ነው ሊወሰድባችሁ የቻለው?

አቶ አንዱአለም፡ አምቦ ላይ 538 የሚሆን ፊርማ ያሰባሰብንበት ሰነድ የተወሰደው በፌደራል ፖሊስ አባል ነው። አዳማ ላይ ደግሞ ፊርማ እያሰባሰቡ የነበሩ ሴት አባሎቻችን ሰነዱን የተነጠቁት የመንግሥት ደጋፊ ነን በሚሉ ሰዎች ነው። በደቡብ ክልል ቡታጅራ የማዘጋጃ ቤት ኃላፊ ነኝ የሚል ሰው 69 ሰው የፈረመበትን ሰነድ ነጥቆ ወሰደ። ጉዳዩን እንደሰማ የፓርቲያችን አስተባባሪ አቶ መሐመድ አሊ መሐመድ ለምርጫ ቦርድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ክትትልና ድጋፍ ክፍል አመልክቷል። አቤቱታችንን በፅሁፍም አስገብተናል።

በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግር አላጋጠማችሁም?

አቶ አንዱአለም፡ ብዙ ፊርማ ያሰባሰብነው ወሎ ውስጥ ነው ምንም ያጋጠመን ችግር የለም። አሁን አስተባባሪዎቻችን በድብቅ ነው ፊርማ እያሰባሰቡ ያሉት።

የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ የሚባል አለ ወይ? የሚሉ አሉ። ትታወቃላችሁ? ማን ነው ደጋፊያችሁ?

አቶ አንዱአለም፡ የድጋፍ መሰረታችን የአንድነት አቀንቃኙ ሕዝብ ነው። በሌላ ፓርቲ ውስጥ እያለንም የምንታወቀው ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነትና ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ በማቀንቀን ነው።

አሁን እኛ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከዚህ ቀደም በ1997ቱ ምርጫ ተሳትፎ የነበራቸው፤ አሸንፈው ፓርላማ የገቡም አሉ።

ፊርማ ያሰባሰብንበት ሰነድ ተነጠቀ የሚለው አቤቱታችሁ ትኩረት ማግኛ ስትራቴጂ ነው ብለው የሚጠረጥሩ ይኖራሉ?

አቶ አንዱአለም፡ይህ ፓርቲያችን ትኩረት ለማግኘት ካዘጋጃቸው መንገዶች መካከል አደለም።

በዚህ ሰዓት ፌደራል ፖሊስን በሐሰት መወንጀል ትልቅ ድፈረት ይጠይቃል፤ እኛም ላይ ኃላፊነትን ያስከትላል። ከዚህ በፊት የፈረምነው የተቃዋሚ ፓርቲዎች የመግባቢያ ሰነድ አለ፤ በምርጫ አዋጁም ይሄ ያስጠይቃል።

እንደዚህ ዓይነት ያለፈበት አካሄድ የሚከተል ስብስብም አደለንም። የተማሩና ልምድ ያላቸው ሰዎች የተሰበሰቡበት ነው። እንዲህ ዓይነቱን ነገር አናስበውም፤ አንሞክረውምም።

ለምን ቀድሞ ከነበራችሁበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (ኢብን) መውጣት አስፈለጋችሁ?

አቶ አንዱአለም፡ኢብንን የመሰረትነው በወቅቱ አደጋ ነው ያልነውን ነገር ከመከላከል አንፃር ነው። በጣም የተጠናከረ የኦሮሞም የአማራም ብሔረተኝነት ነበር። ይህን ለመከላከል ደግሞ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በለዘብተኝነት ሳይሆን በተመጣጣኝ ኃይል የሚያቀነቅን ቡድን መፍጠር ያስፈልጋል ብለን ነበር የተነሳነው።

የዛሬ ሁለት ዓመት እና ሁለት ዓመት ተኩል ገደማ በሚያስፈራ ሁኔታ ኢትዮጵያዊነት የወደቀበት ጊዜ ነበር። አሁን ግን ኢትዮጵያዊነት አፈር ልሶ እየተነሳ ነው። ስለዚህ ይህንን ለማስቀጠል ጥያቄ የሚያነሱ አካላትን ጥያቄ በዘላቂነት የሚመልስ፤ ቅራኔያቸውንም በዘላቂነት የሚፈታ አካሄድ ማምጣት ነው ያለብን ብለን ስላሰብን ነው።

አማራነት፣ ኦሮሞነት. . . የለም ብለን በኃይል የሄድንበት መንገድ ምናልባት ትክክለኛ ነው ብለን ብናምንም ጊዜው ግን አሁን አይደለም። ስለዚህ እንደ ሽግግር ተራማጅ የሆነ ሃሳብ ለማራመድ ወስነናል፤ ወደ ተነሳንበት እንመለሳለን አሁን ግን ጊዜው አይደለም። ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነታችንን ግን አንክድም።

ሲደረግ የነበረው ከዚህ በፊት አንድ ነን ልዩነትም የለንም፤ ኢትዮጵያ አንድ ነች የሚል አካሄድ ነበረ። እሱ አያዋጣም የሚደረስበት ወደፊት ነው። የሙስሊሙን፣ የኦሮሞውን፣ የኦሮሚያ ቤተክህነት እናቋቁም የሚሉም ብዙ ጥያቄ የሚያቀነቅኑ ስብስቦችን ማዳመጥ ያስፈልጋል።

እንደ ከዚህ ቀደሙ ፀብ የማብረድ ዓይነት ሳይሆን እነዚህ ስብስቦችን ለየት ባለ አረዳድ ከሰማናቸው በኋላ ነው አገር መመስረት የሚቻለው።

ለየት ያለ ተራማጅ አሰማም እንዴት ያለ ነው?

አቶ አንዱአለም፡ተራማጅ አሰማም ማለት ዘመኑን የዋጀ አሰማም ማለት ነው። አሁን ለጥያቄዎች በአንድ ዓይነት መንገድ ነው ምላሽ እየተሰጠ ያለው። መልስ የጠፋው ጥያቄዎቹን የምናይበት አግባብ ችግር ያለው ስለሆነ ይሆናል።

ተራማጅነት ማለት እነዚህን ጥያቄዎች መቀበል ማለት አይደም። ጥያቄያቸውንም ለማድመጥ ፍቃደኛ መሆን እና ተቀራርቦ መስራት ነው። የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ስብስቦችን ከጅምሩ አቀራርቦ ይዞ የሚሄድና መዳረሻውን ኢትዮጵያዊነት ያደረገ አካሄድ ነው።

አካሄዱ ግን የሚያዋጣ ነው ብላችሁ ታስባላችሁ?

አቶ አንዱአለም፡ አይመስልም ግን የያዝነው ትግል ነው። ትግል ደግሞ የሚሆን የማይመስለውን ነገር ሁሉ ታግሎ ማስቻል ነው። ቀላሉን ብቻ ሳይሆን የማይቻለውንም ታግሎ ማስቻል ይቻላል።

የእኛ ሃሳብ አብዛኛው ዝም ያለው ሕዝብ ጋር ነው ያለው ብለን እናስባለን። ፅንፈኛ ሃሳብ የሚያራምዱትን ትቶ ለእኩልነት የሚሆን በቂ ሃሳብ ማራመድ የሚችል ኦሮሞ፣ አማራም አለ።

እንደ አንተ ያሉ በማህራዊ ሚዲያ የሚታወቁ ወጣቶች በፓርቲው እንዳሉ ገልፀህልኛል። አንተን ራሱ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባለህ ተሳትፎ ብትቀጥል ይሻላል የሚል ብዙ አስተያየት አለ። በዚሁ ምክንያት ፓርቲያችሁን በቁም ነገር መውሰድ የሚቸግራቸው ሰዎች አሉ?

አቶ አንዱአለም፡ እውነት ነው የእኔ የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳትፎ የተወሰነ ተፅእኖ ማድረጉ አይቀርም። ሰዎች ከእኔ የሚጠብቁት ነገር አለ፤ እኔም ራሴ ከራሴ የምጠብቀው ነገር አለ።

ለውስጤ ቅርብ የሆነው ሥነ ፅሁፍ ነው ፖለቲካው ከሞላ ጎደል ተገድጄ የገባሁበት ነው። እንደ አብንና ጃዋር ያሉ አካላት ያላቸውን ነገር ተጠቅመው አገርን እንደፈለጉ ለማድረግ በሚሰሩበት ሰዓት እኔ ቁጭ ብዬ በአሽሙርና በሥነ ፅሁፍ መንግሥትን መጎንተል ተገቢ ነው ብዬ አላመንኩም።

ተራማጅ ፓርቲ ዛሬ ባለው ቅርፅ ወደ መሬት ከወረደ ገና አምስት ወሩ ነው። በምርጫው ምን ያህል ይራመዳል?

አቶ አንዱአለም፡ ስም መጥራት አንፈልግም እንጂ ከተመሰረቱ ብዙ የቆዩ ግን በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ፓርቲዎች አሉ። ስለዚህ ዋናው ነገር የጊዜ ጉዳይ አይደለም፤ እኛ የምናሳትፋቸው እጩዎች ልምድ ያላቸው ፖለቲከኞች ናቸው።

የምትወዳደሩት የት የት ነው?

አቶ አንዱአለም፡ በእርግጠኝነት አማራ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና አዲስ አበባ ላይ እንወዳደራለን።

የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ የወጣቶች ፓርቲ ነው?

አቶ አንዱአለም፡ ወጣት ይበዛዋል ግን ልምድ ያላቸው ትልልቅ ሰዎችም አሉ። ስንጀምር ገና አደረጃጀት ስንሰራ ለየት እንበል በሚል ዲግሪ እና ከዚያ በላይ ያላቸውን ነው አባልት ያደረግነው።

መመስረቻ ምርሃ ግብር ስናካሂድ 250 ሰዎች ተገኝተው የነበረ ሲሆን 230 የሚሆነው ወጣት ነበር።

ከዚህ ውስጥ 200ው ማስትርስ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸው ነበሩ። ኮሌጅ ብታቋቁሙ ይሻላል ተብሎ ተቀልዶ ሁሉ ነበር። በዚያ መንገድ መቀጠል ስለማይቻል ግን አሁን ሁሉንም ሰው እያሳተፍን ነው።

ከምርጫ በኋላ በዚህ መስፈርታችሁ ልትቀጥሉ ትችላላችሁ?

አቶ አንዱአለም፡ አዎ እኛ ልንፈጥር ያሰብነው የምርጫ ፓርቲ አይደለም። ቀስ ብለን የጥናት ቡድን አደራጅተን፤ ተጠንቶ መንግሥትን በፖሊሲ የሚሟገት ትልቅ ፓርቲ መፍጠር ነው የፈለግነው። በዚህ ምርጫ ለምን አስር ወንበር አናገኝም ችግር የለውም።