አሜሪካ የቀድሞውን የናዚ ማጎሪያ ካምፕ ጠባቂን ከ75 ዓመት በኋላ ወደ ጀርመን ልትልክ ነው

ከናዚ ማጎሪያ ካምፖች አንዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ የሚመለከት የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ሬቤካ ሆልት የናዚዎች አይሁዶችን ያሰቃዩበት የነበረን ካምፕ የቀድሞ ጠባቂ የነበሩት የዛሬው የ94 ዓመቱ አዛውንት ፍሬድሪክ ካርል በርገር በግድ ወደ ጀርመን እንዲላኩ ውሳኔ አስተላለፉ።

በርገር በማጎሪያ ካምፑ የሰሩት ታዝዘው እንጂ በፍላጎት እንዳልነበር ለዋሽንግተን ፖስት ተናግረዋል።

አዛውንቱ በርገር ቢያንስ ተገድደው ወደ ጀርመን የሚወሰዱበትን ጊዜ ለማራዘም ለፍርድ ቤቱ ይግባኝ ይጠይቁ እንደሁ የታወቀ ነገር የለም።

ለዘመናት አሜሪካ የኖሩት አዛውንቱ በርገር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ "ከ75 ዓመታት በኋላ፣ ይህ የሚገርም ነው ለማመንም ይከብደኛል። ከቤቴ እኮ ነው በግድ እያስወጣችሁኝ ያላችሁት" ብለዋል።

አዛውንቱ የቀድሞ የናዚ ካምፕ ጠባቂን ጉዳይ የተመለከተው ችሎት ሃሙስ እለት የተሰየመው በሜሚፊስ ነበር።

ዳኛዋ በበኩላቸው "የናዚ ጭፍጨፋ በተካሄደበት ካምፕ በፍቃደኝነት የጥበቃ አገልግሎት መስጠት በናዚ ጭፍጨፋ እንደመተባበር ይቆጠራል" ብለዋል።

ችሎት ሲሰማ አዛውንቱ በርገር ከካምፕ ለማምለጥ ይሞክሩ የነበሩ እስረኞችን ሲመልሱ እንደነበር አምነዋል። ነገር ግን በካምፑ የጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ለአጭር ጊዜ እንደሆነና መሳሪያም ይይዙ እንዳልነበር ለማስረዳት ሞክረዋል።

ዳኛዋ ለሁት ቀን በተካሄደው የአዛውነቱ ችሎት ስሚ ላይ ፌዝ በሚመስል መልኩ "እስካሁንም በጦርነት ወቅት ላበረከተው አገልግሎት ጡረታ እያገኘ ወዳለበት ጀርመን እንዲሄድ ይደረጋል" ብለዋል።