በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሴሪ አ ውድድሮች ካለተመልካች ሊካሄዱ ነው

በሽታውን ለመካላከል መድሃኒት ሲረጭ

የፎቶው ባለመብት, EPA

በኮሮናቫይረስ በአውሮፓ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በሞተባት በጣሊያን የሴሪ አ እግር ኳስ ግጥሚያዎችን ጨምሮ ሁሉም የስፖርት ውድድሮች ለአንድ ወር ያህል ለተመልካች ዝግ ሆነው እንደሚካሄዱ ተገለጸ።

በተጨማሪም መንግሥት በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ያለውን ይህንን በሽታ ለመግታት ሲል ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለ10 ቀናት እንዲዘጉ አዟል።

በአውሮፓዊቷ ጣሊያን ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መቀስቀሱ ከታወቀ በኋላ የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ 197 መድረሱ ተነግሯል።

የአገሪቱ ባለስልጣናት እንደገለጹት በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ 49 ሰዎች በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል። በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ4600 በላይ ደርሷል።

በኅዳር ወር የበሽታው ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰባት ቻይና ቀጥሎ ጣሊያን ብዙ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የሞተባት አገር ሆና ተመዝግባለች።

የዓለም የጤና ድርጅት እንዳለው እስካሁን ድረስ በሽታው በተገኘባቸው አገራት ውስጥ 100 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል።

ከዚህ ሁሉ የባሰው ደግሞ በአራት ወር ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ሲሞቱ አብዛኛው ሞት ያጋጠመው ደግሞ ቻይና ውስጥ መሆኑ ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክትር ቴድሮስ አድሃኖም የበሽታውን መስፋፋት "በጣም አሳሳቢ" በማለት የገለጹት ሲሆን ሁሉም አገራት ወረርሽኙን መግታት ቀዳሚና ዋነኛው ተግባራቸው እንዲሆን ጠይቀዋል።

የጣሊያን ባለስልጣናት ከፍተኛውን የሟቾች ቁጥር ይፋ ያደረጉት ትናንት ነው።

የጣሊያን ብሔራዊ የጤና ኢንስቲቲዩት እንዳለው የሞቱት ሰዎች አማካይ ዕድሜ 81 ሲሆን አብዛኞቹ ሌላ የጤና ችግር የነበረባቸው ነበሩ። ከሟቾቹ ውስጥም 72 ከመቶ የሚሆኑት ወንዶች ናቸው።

ጣሊያን በዓለም ላይ በርካታ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ከሚኖሩባቸው አገራት መካከል አንዷ ናት።