የኢትዮጵያው አውሮፕላን አደጋ ረቂቅ ሪፖርት ቦይንግን ተጠያቂ አደረገ

አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአንድ ዓመት በፊት የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ምክንያት የአውሮፕላኑ የዲዛይን ችግር እንደሆነ መርማሪዎች ለአሜሪካ መንግሥት መስሪያ ቤቶች ያዘጋጁት የአደጋው ረቂቅ ሪፖርት አመለከተ።

ሮይተርስ እንደዘገበው የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ ቅሬታ ወይም እንዲለወጥ የሚያቀርበው ሃሳብ ካለው ዕድል እንደተሰጠው፤ ሪፖርቱ ይፋ ስላልተደረገ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሰዎች ተናግረዋል።

የቦርዱ ቃል አቀባይ ኤሪክ ዌይስ ጊዜያዊው ረቂቅ ሪፖርትን እንደተቀበሉ ቢገልጹም ድርጅታቸው ለውጥ እንዲደረግ ይጠቅ እንደሆነ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። ቦይንግ ሪፖርቱን በተመለከተ ምላሹ ምን እንደሆነ በሮይተርስ ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

ረቂቅ ሪፖርቱን ቀድሞ ይፋ ያደረገው ብሉምበርግ ኒውስ እንዳለው የሪፖርቱ ማጠቃለያ ስለኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ የበረራ ሰራተኞቹ አሰራርን በተመለከተ ውስን ወይም ምንም ነገር ባለማለቱ በምርመራው ላይ በተሳተፉ አንዳንድ ሰዎች ዘንድ ጥያቄን አስነስቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት በነበረው አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ በተመለከተ የተዘጋጀው ረቂቅ ሪፖርት፤ በአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ላይ በነበረ ችግርና በአብብራሪዎች ስህተት እንደተከሰከሰ በተነገረለት በተመሳሳዩ የኢንዶኔዢያው የላየን ኤር አውሮፕላን ሪፖርት ጋር መነጻጸሩ ተገልጿል።

ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ ለመጓዝ ከአዲስ አበባ ከተነሳ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር 302 የአውሮፕላኑ ሰራተኞችን ጨምሮ 157 ሰዎች ሞተውበታል።

ከዚህ አሰቃቂ አደጋ በኋላም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ እንዲሆኑ ተደርጓል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የበላይ ተቆጣታሪነት ስር ካናዳ ሞንትሪያል በሚገኘው የአቪዬሽን ኤጀንሲ ደንብ መሰረት፤ ኢትዮጵያ አደጋውን በተመለከተ የመጨረሻውን ሪፖርት በአደጋው አንደኛ ዕለት ይፋ ማድረግ ይኖርባታል።

32 ኬንያዊያን፣ 18 ካናዳዊያን፣ 18 ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ የ33 አገራት 157 ዜጎች ህይወታቸው ያለፈበትን የዚህን አደጋ አንደኛ ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጪው ማክሰኞ አስቦት እንደሚውል ቢቢሲ አረጋግጧል።